ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ኃይል ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራና በታዳሽ ኃይል ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለአፍሪካውያን በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር "የአጀንዳ 2030 እና 2063 ግቦችን ለማሳካት የተቀናጀና አሻጋሪ አካሄድ መከተል" በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው 12ኛው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።

በየዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ጉባኤ የአፍሪካ ሕብረትን የአጀንዳ 2030 እና 2063 የዘላቂ የልማት ግቦችን አፈፃፀም ለመገምገም ነው።

የአፍሪካ ሕብረት "የምንመኛትን አፍሪካ" እውን የማድረግ ግብ ለማሳካት በመንግሥታትና በአጋር አካላት መካከል ያለውን ትብብርና ቅንጅታዊ አሠራር መገምገም ያስችላል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ እና በኢ-ተገማች የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ተስፋና ሥጋት እያስተናገደች ነው።

በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው፣ አካታችና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት አህጉራዊ ለውጥና ሽግግር ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢነርጂ፣ መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ ከተማ ከማዘመን ባለፈ በሀገራት መካከል የእሴት ትስስር መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ እርምጃ እየወሰደች መሆኑን በመግለፅ፤ ለአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ግብ መሳካት ገንቢ ሚና አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የደን ሽፋኗን ለማሳደግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከሏን አስታውሰው፤ በዓለም የደን ልማት ዘርፍ ከፍተኛው ኢኒሼቲቭ መሆኑን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ 90 በመቶ ኃይል ከታዳሽ ኃይል የሚገኝ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝነት አለው ነው ያሉት።

በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ ኃይልና ከተማ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶች ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ሀገራት ዘላቂ ዕድገት ገንቢ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ኢኒሼቲቮቹ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም የውኃ ደህንነትን ማረጋገጥ እንደያስችሉ ጠቁመዋል።

የአፍሪካን የረጅም ጊዜ የልማት ዕቅዶች እና የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

አፍሪካ የአጀንዳ 2030 እና 2063 ዘላቂ ግቦችን ለመፈጸም በምታደርገው ጥረት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም