ቀጥታ፡

የታዳሽ ኃይልና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልማት ጉዞዎች የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን ዕድል ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልማት ጉዞዎች የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን ዕድል መፍጠራቸውን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት መስኮች ዕድገቷን የሚያፋጥን ጉዞ ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗን አምባሳደሩ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በተለይም በታዳሽ ኃይልና በቴክኖሎጂ ሽግግር የምትፈጥረው አስደናቂ ዐቅም ለታዳጊ ሀገራት ጭምር ተሞክሮ የሚቀሰምበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልማት ጉዞዎችም የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥኑ ወሳኝ ዘርፎች መሆናቸውን አንስተዋል።

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የፈጠረችው የኃይል ትስስርም የጋራ ኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን ትኩረት የሚሰጠው የልማት መርሐ-ግብር መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ፈረንሳይም ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማትን ለማስፋት በምታደርገው ጥረት አስፈላጊውን የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለዲጂታላይዜሽን መሠረተ ልማት መስፋፋት የሰጠችው ትኩረት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል አምባሳደሩ።

የዲጂታል ምርታማነት ዐቅምን የበለጠ ለማጎልበት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በተቋም ደረጃ መገንባቷንም አድንቀዋል።
ለዲጂታል ልማት የተሰጠው ትኩረት፤ የቴክኖሎጂ ጀማሪ ኩባንያዎችን በማበረታታት የፈጠራ ክህሎትና ተነሻስነትን እያጠናከረ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም