ቀጥታ፡

የጤና መከላከልና አክሞ ማዳን የፖሊሲ እርምጃ ጤናማ ዜጋ ማፍራት የሚያስችል ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የጤና መከላከልና አክሞ ማዳን የፖሊሲ እርምጃ አምራችና ጤናማ ዜጋ ማፍራት የሚያስችል ውጤት እያስገኘ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ሳህረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሀገራዊ ለውጡ ዓመታት የጤና ተቋማትን ዐቅም በማጎልበት በሽታ መከላከልና አክሞ ማዳን ጥምርታ ተጨባጭ ውጤት መጥቷል።

የኢትዮጵያን የጤና መከላከልና አክሞ ማዳን የፖሊሲ እርምጃ ቅንጅታዊ ዐቅም በማጎልበት፤ አምራችና ጤናማ ዜጋ ማፍራት የሚያስችል ውጤት መምጣቱንም ገልጸዋል።

ከጤና ኬላ እስከ ሪፈራል ሆስፒታል ድረስ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችም፤ የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት በማስፋት የዜጎችን የጤና ፍላጎት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የጤና ባለሙያዎችን ዐቅም ለማጎልበትም በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት የትምህርት ዕድል በማመቻቸት ክኅሎታቸውን እንዲያሳድጉ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የጤና ተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራትም፤ የእናቶችና ሕፃጻትን ሞት በመቀነስ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ምጣኔ ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።

በጤና ኬላ የሚሰጡ የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ-ግብሮችንም ወደ አጠቃላይ የጤና ማዕከልነት በማሸጋገር ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም የሪፈራል፣ የክትባት፣ የእናቶች የወሊድ ክትትልን ጨምሮ ሌሎችን ዘመናዊ አገልግሎቶች በማስፋት ለሕብረተሰቡ በቅርበት እየሰጡ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዲጂታል ኢትጵያ-2025 ስትራቴጂ የተፈጠረውን የዲጂታል የጤና ዐቅም በዲጂታል ኢትዮጵያ-2030 የበለጠ ለማጎልበት ትኩረት መደረጉንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም