ከ140 ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን ከምዝበራ ማዳን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ከ140 ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብትን ከምዝበራ ማዳን ተችሏል
ቦንጋ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ140 ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ከምዝበራ ማዳንና ማስመለስ መቻሉን የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ እንዳሉት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 748 የሙስና ጥቆማዎችን በመቀበል በ97ቱ ላይ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ ተሠርቷል።
እንዲሁም 134ቱ ጥቆማዎች ለፍትሕ አካላት እንዲተላለፉ መደረጋቸውን ገልጸው፤ ሌሎች 269 የሙስና ጥቆማዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 76 መዝገቦች በሂደት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በተከናወነ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራና የኦዲት ግኝት ከ140 ሚሊየን 742 ሺህ ብር በላይ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለማዳንና ለማስመለስ መቻሉን ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
ለማዳን ከተቻለው ገንዘብም 81 ሚሊየን 550 ሺህ ብሩ በኦዲት የተገኘ እና ቀሪው ገንዘብ በቅድመ መከላከል ለማዳን የተቻለ መሆኑን አብራርተዋል።
ከገንዘብ በተጨማሪ 13 ሺህ 673 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ እና 1 ሺህ 380 ሔክታር የገጠር መሬት ከምዝበራ ማዳን ተችሏል ብለዋል።
የሀብት ምዝገባ ሥራ ሙስናን መከላከያ አንዱ መንገድ መሆኑን አስገንዝበው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራትየ 1 ሺህ 285 አዲስ ሠራተኞችን እና 120 ከፍተኛ አመራሮችን ሀብት የመመዝገብ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።