ቀጥታ፡

ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

ነገሌ ቦረና፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ቦረና በዞን በለውጡ ዓመታት ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ ገንዘብ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

በጽሕፈት ቤቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ዕቅድና በጀት፣ ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ ሊበን አና ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዞኑ በመከናወን ላይ ያሉ 145 ፕሮጀክቶች የማሕበረሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች የሚፈቱ ናቸው።


 

ከነዚህም መካከል ስምንቱ ከፍተኛ ፕሮጀክቶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ በግንባታ ላይ የሚገኙ 21 የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማትና የመስኖ ፕሮጀክቶችን መኖራቸውንም አመላክተዋል።

ዘጠኝ የገጠር መንገዶች፣ 16 የጤና ተቋማትና 11 የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ነው የገለጹት።


 

በአሁኑ ወቅትም 37 የግንባታ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጸው፤ የ47 ፕሮጀክቶች ግንባታ 90 በመቶ መድረሱን አረጋግጠዋል።

ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በለውጡ ዓመታት የዞኑን ሕዝብ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩት የልማት ሥራዎችተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል።

የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ከ800 ሺህ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ የማድረግ ዐቅም እንደሚኖራቸውም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም