በጭሮ ከተማ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጭሮ ከተማ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው
ጭሮ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን የከተማው የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ንግድ ጽሕፈት ቤት ገለፀ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አደም ዩሱፍ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በከተማዋ የንግድ ሥርዓቱን ቀልጣፋና ሕጋዊነቱን ለማረጋገጥ ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀትና ግብረ ኃይል በማቋቋም እየተሠራ ነው።
በዚህም ያለ ንግድ ፈቃድ በሚሠሩና አሳማኝ ባልሆነ መንገድ ዋጋ በመጨመር ሕብረተሰቡን በሚያማርሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርመጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ለአብነትም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሸቀጦች ላይ ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ፣ የሸቀጥ ዋጋን በግልፅ ቦታ ያልለጠፉ እና ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶችን ሲሸጡ የተገኙ 141 ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን ጠቅሰዋል።
የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን በተከናወኑ ተግባራት 748 ግለሰቦች ወደ ሕጋዊ ሥርዓቱ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።
የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ ጀማል ቃሲም በበኩላቸው፤ በዞኑ 15 ወረዳዎችና አምስት ከተሞች የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከሕብረተሰቡ አስተያየቶችን በማሰባሰብ መንግሥት ድጎማ የሚያደርግባቸው እንደ ነዳጅ፣ ስኳር እና ዘይት ያሉ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።