ቀጥታ፡

የቅርስ ጥበቃና ዕድሳት ስኬት ዘርፉ በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ገንቢ ሚና የሚወጣበትን ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃና ዕድሳት ስኬት ዘርፉ በሀገር ገፅታ ግንባታና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ገንቢ ሚና የሚወጣበትን ዕድል መፍጠሩን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ገለጸ።  

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የኢትዮጵያን ቅርሶች ደኅንነት የሚያስጠብቅ መጠነ-ሰፊ የልማት ሥራ ተሠርቷል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ዕድሳት፣ ጥበቃና የልማት ሥራም ጎስቋላ ገፅታን በመላበስ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸው የነበሩ የሀገር ምልክቶችን መታደግ እንዳስቻለ ገልጸዋል።

የቅርስ ዕድሳቱም የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ለበርካታ ዓመታት የቆዩ የነገሥታት መኖሪያና የአስተዳደር ሕንፃዎችን ይዘት በማስጠበቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።

ተዘርፈው የነበሩ የኢትዮጵያ ጥንታውያን መጻሕፍትና ቅርሳ ቅርሶችንም ወደሀገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ ለጎብኝዎች ክፍት እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የአፄ ፋሲለደስ ቤተ-መንግሥታት፣ የሶፍ ዑኡመር ዋሻና የጅማ አባጅፋር ቤተ-መንግሥት፣ የጀጎል ግንብ መሰል ቅርሶች ዕድሳት እንደተደረገላቸው አብራርተዋል።

የሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ዕድሳትም የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ለኢኮኖሚ ዕድገት ገንቢ ሚና እንዲያበረክቱ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ፣ ዕድሳትና ልማት ሥራ በሀገር ገፅታ ግንባታና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ገንቢ ሚና የሚወጣበትን ዕድል መፍጠሩንም አክለዋል።

በተለያዩ ክልሎች በቅርስ ጥበቃና ልማት ሥራ የተገነቡ ሙዚየሞችም በግለሰቦችና ድርጅቶች እጅ የነበሩ ታሪካዊ ቅርሶች ዘላቂ ማረፊያ የሚያገኙበትን ዕድል መፍጠር እንደቻሉ አስረድተዋል።

ይህም ትውልድ በታሪካዊ ቅርሶች ላይ ትምህርት የሚቀስምበትን ወሳኝ ዕድል እንደፈጠረ ጠቅሰዋል።

የዲጂታል የቅርስ ጥበቃና አገልግሎትም የቅርስ ምዝገባ፣ ፈቃድ አሰጣጥ፣ ሙዚየም አገልግሎትና የክፍያ ሥርዓቱን በማዘመን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም