ቀጥታ፡

በመዲናዋ የሰው ተኮር ልማትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስኬቶች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የሰው ተኮር ልማት ፕሮጀክቶችና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የተተገበሩ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጡ መሆናቸውን የተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።

ከሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሥራ አፈፃጸም ግምገማ ተጠናቋል። 


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የአገልግሎት አሰጣጡን በመሠረታዊነት የሚቀይሩ የቴክኖሎጂ፣ የአሠራርና የሰው ኃይል ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። 
 
በተለይም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዮችን ጊዜ፣ ወጪና እንግልት በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡንም ጠቁመዋል፡፡
 
የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፤ በንግድ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በኑሮ ውድነት ማረጋጋትና በንግድ ሕግ ተገዢነት ላይ ከፍተኛ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።


 

የግንዛቤ ፈጠራና የአስተዳደራዊ እርምጃዎች ውጤት እያመጡ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ በሀገራዊ አቅጣጫ መሠረት የነዳጅ አጠቃቀም ላይ መስተጓጎል እንዳይኖር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
የትራንስፖርት ዘርፉ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ካለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያብባል አዲስ ናቸው።


 

በትራፊክ ማኔጅመንት፣ በመንገድ ደኅንነትና የተሽከርካሪዎችን ፍጥነት በመቀነስ ረገድ አመርቂ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዘሪሁን አባተ (ኢ/ር)፤ በከተማዋ የውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎትን ለማሻሻል መጠነ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡



 
በቀጣይም የኅብረተሰቡን እርካታ ይበልጥ የሚያረጋግጡ የተሻሉ አገልግሎቶችን ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም