የጥጥ ልማት በአፋር - ትልቅ ዐቅምን ወደ ምርታማነት የመቀየር አዲስ ጥረት - ኢዜአ አማርኛ
የጥጥ ልማት በአፋር - ትልቅ ዐቅምን ወደ ምርታማነት የመቀየር አዲስ ጥረት
ሰመራ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- የአፋር ክልል ያለውን ሰፊ የጥጥ ልማት ዐቅም ወደ ተሻለ ምርታማነት ለመቀየርና ዘርፉን በላቀ ደረጃ ለማልማት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሀገሪቱ እየተተገበረ ያለው የብዝኀ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ክልሎች በራሳቸው ፀጋ ላይ ተመስርተው እንዲለሙ ሰፊ በር ከፍቷል።
ይህ ፀጋን ለይቶ የማልማት ጥረትም የክልሎችን የኢኮኖሚ ዐቅም ከማሳደጉም በላይ፤ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጠ ነው።
የአፋር ክልል የበርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ቢሆንም፤ እነዚህን እምቅ ሀብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት በመቀየር ረገድ ለረጅም ዓመታት ክፍተቶች ሲታዩ ቆይተዋል።
ሆኖም አሁን ላይ እነዚህን ያልተነኩ ፀጋዎች ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሳምሶን አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአፋር ክልል ጥጥን በመስኖ ማልማት የሚያስችል ዐቅም ስላለው ልማቱን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።
በዚህም ከባለሀብቶች በተጨማሪ አርብቶ አደሩና ከፊል አርሶ አደሩ በልማቱ መሰማራት እንዲችሉና ክልሉ ያለውን የመልማት ዐቅም ተግባር ላይ ለማዋል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሀገር የጥጥ ልማትን ለማስፋፋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ በ2017/18 የምርት ዘመን በስድስት ክልሎች 110 ሺህ ሔክታር መሬት በጥጥ መልማቱን ተናግረዋል።
በዚህም 79 ሺህ ሜትሮክ ቶን የተዳመጠ ጥጥ በማምረት ለኢንዱስትሪዎች ማቅረብ መቻሉን ገልፀው፤ ተወዳዳሪ እና ጥራት ያለው ምርት ለማምረት የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚጠናከሩ አረጋግጠዋል።
የአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ያሲን ዓሊ (ኢ/ር) እንዳሉት፤ አፋር በጉልህ የሚታወቅበትን የጥጥ ሀብት መልሶ ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የክልሉ የጥጥ ምርት ጥራት ያለውና ለውጭ ገበያ ተወዳዳሪ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ ለመሰማራት ለሚሹ ባለሀብቶችና ለአካባቢው አርብቶ አደሮች ምቹ የሥራ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
በአፋር ክልል የሚገኘው ለም መሬት ካለምንም ተጨማሪ ማዳበሪያና ኬሚካል ለጥጥ ልማት ተስማሚ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የ"ኦርጋኒክ ኮተን ፕሮጀክት" አስተባባሪ መሰለ መኩሪያ ናቸው።
ይህን ዐቅም ወደ ውጤት ለመቀየር እየሠሩ መሆኑን አንስተው፤ የልማቱ መጠናከር ለክልሉም ሆነ ለሀገር ይዞ የሚመጣው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ግብርና ሚኒስቴር ከአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ጋር በመተባበር በአውሲ ረሱ ዞን የጥጥ ልማትን እንደገና ለማስፋፋት የሚያስችል የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩም፤ በዱብቲ፣ አይሳኢታ፣ አፋምቦና ገረኒ ወረዳዎች የሚገኙ እምቅ የልማት አማራጮችን በመጠቀም በተለይም የተፈጥሮ ጥጥ ምርትን (Organic Cotton) ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሠራ ተመልክቷል።