በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ16 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን ከ16 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
ገንዳ ውኃ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን የአካባቢን ጸጋ በመጠቀም 16 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ ሥራና ክኅሎት መምሪያ ኃላፊ ኤፍሬም ወርቁ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ 24 ሺህ ወጣቶችን በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሠሩ ሥራዎች 16 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ኃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።
የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡም ከአጋር ድርጅቶችና ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ከ225 ሚሊየን ብር በላይ ብድር መሠራጨቱን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ለሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ በማመቻቸት ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተፈጠረው የሥራ ዕድልም ባለፈው በጀት ዓመት ከተፈጠረው ጋር ሲነጻጸር ከ2 ሺህ በላይ ብልጫ አለው ብለዋል።
የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ቅዱስ ተወልደ እንደገለጸው፤ ተቀጥሮ ሲሠራበት ከነበረ የግለሰብ ድርጅት ወጥቶ በቤትና በቢሮ ዕቃዎች ማምረት ዘርፍ የራሱን የሥራ ዕድል ፈጥሮ እየሠራ ነው።
በቂ ብድርና ተከታታይ ድጋፍ ተደርጎልናል ያለው ወጣቱ፤ በቀጣይም ሥራውን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አስደግፎ በማከናወን ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
በመተማ ወረዳ በዘላቂ ተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የሥራ ዘርፍ የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት አደም ሙሀመድ በበኩሉ፤ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በእጣንና ሙጫ ማምረት ሥራ ተሰማርተው ውጤታማ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጿል።
የአካባቢያቸውን ሥነ-ምኅዳር በጠበቀ መንገድ ከሚያመርቱት የእጣን ምርት ሽያጭ ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩ ገልጾ፤ በእጣን ምርት አመራረትና ተያያዥ ተግባራት ዙሪያ የተደረገላቸው የዕውቀት ሽግግርም የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አመላክቷል።