ቀጥታ፡

በጅማ ከተማ በማኅበር ለተደራጁ ከ28 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል

ጅማ፤ ሚያዝያ 20/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዘጠኝ ወራት በማኅበር ለተደራጁ ከ28 ሺህ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የጅማ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ክኅሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱልሀሚድ ኑረዲን ገለጹ።

የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  የብድር አገልግሎት ማመቻቸትና የገንዘብ አያያዝ ሥልጠና እንዲሁም የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎች መመቻቸቱን ኃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።

 ይህን ድጋፍ በማቅረብም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ለ28 ሺህ 811 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አረጋግጠዋል።
 
ወጣቶቹ በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ውጤታማ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑም ገልጸዋል።

በማኅበር የተደራጁት ወጣቶች ገቢያቸውን ከማሳደግ ባለፈ የቁጠባ ባህልን በማዳበር ሽግግር የሚያደርጉበትን ዐቅም ለመፍጠር በቅንጅት መሠራቱንም አንስተዋል።

ከጎደኞቿ ጋር በመደራጀት ምንጣፎችን በማምረት ሥራ ላይ መሰማራቷን የገለጸችው ሄርሜላ ስሜነህ፤ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ብድር በመውሰድ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድታለች።


 

ከተማ አሥተዳደሩ ያመቻቸላቸው የማምረቻ ቦታ፣ ድጋፍና ክትትል በሥራቸው ትርፋማ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ጠቁማ፤ ሥራቸውን  የበለጠ ውጤታማ  በማድረግ  ወደ ኢንቨስትመንት ለመሸጋገር ከወዲሁ አቅደው እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግራለች።

አብርሀም በለጠም ከጓደኞቹ ጋር በመደራጀት የቡና መፈልፈያ ማሽኖችን እየሠሩ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድቷል።


 

ማሽኖችን ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለሌሎች ወጣቶች  የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም አስታውቋል።

በጂብሰም እና ፋይበር ሥራ ላይ ተደራጅተው ውጤታማ በመሆን ለሌሎች ወጣቶች አርዓያ መሆናቸውን ያነሳው ደግሞ ብሩክ በቀለ ነው።


 

ሥራቸውንም ለማሳካት ከተማ አሥተዳደሩ የመሥሪያና የብድር አቅርቦት በማመቻቸቱ  ለ12 ሰዎች  የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም