የኃያላኑ ፍጥጫ፦ ፒኤስጂ ከባየር ሙኒክ - ኢዜአ አማርኛ
የኃያላኑ ፍጥጫ፦ ፒኤስጂ ከባየር ሙኒክ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 20/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ፒኤስጂ ከባየር ሙኒክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በፓርክ ደ ፕሪስንስ ስታዲየም ይካሄዳል።
በሩብ ፍጻሜው ፒኤስጂ ሊቨርፑልን፣ ባየር ሙኒክ ሪያል ማድሪድን አሸንፈዋል።
ሁለቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ16ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 15 ጨዋታዎች ፒኤስጂ በዘጠኙ ሲያሸንፍ ባየር ሙኒክ ስድስት ጊዜ ድል ቀንቶታል።
በ15ቱ ጨዋታዎቹ ላይ ፒኤስጂ 21 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ የጀርመኑ ክለብ 16 ግቦችን አስቆጥሯል።
ክለቦቹ ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024/25 በሊግ እርከን ምዕራፍ (League phase) ነው።
በወቅቱ ባየር ሙኒክ በሚንጄ ኪም ጎል 1 ለ 0 አሸንፏል።
እ.አ.አ በ2019/20 በፍጻሜው ተገናኝተው ባየር ሙኒክ 1 ለ 0 በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።
እ.አ.አ በ1994 በሻምፒዮንስ ሊጉ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ፒኤስጂ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ድንቅ ግስጋሴ እያደረገ የሚገኘው ባየር ሙኒክ የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ስድስት ጊዜ አንስቷል።
ፒኤስጂ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ነው።
ጨዋታው ተመጣጣኝ እና አዝናኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።