ማንችስተር ዩናይትድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ጫፍ ያደረሰውን ወሳኝ ድል አስመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ዩናይትድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ጫፍ ያደረሰውን ወሳኝ ድል አስመዘገበ
አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት ማንችስተር ዩናይትድ ብሬንትፎርድን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ማምሻውን በኦልድትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካሲሚሮ እና ቤንጃሚን ሼስኮ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ማቲያስ የንሰን ለብሬንትፎርድ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ማንችስተር ዩናይትድ ያገኛቸውን የግብ እድሎች በሚገባ መጠቀሙ አሸናፊ አድርጎታል።
በኳስ ቁጥጥር የተሻለ የነበረው ብሬንትፎርድ ያገኛቸውን እድሎች ተጠቅሞ ተጨማሪ ጎሎች ማስቆጠር አልቻለም።
ጨዋታው አዝናኝ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል።
በሊጉ 17ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ዩናይትድ በ61 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ዩናይትድ የሻምፒዮንስ ሊጉን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ይበልጥ ተቃርቧል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ 12ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ብሬንትፎርድ በ48 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ለቤንጃሚን ሼስኮ ግብ መቆጠር ምክንያት የሆነው ብሩኖ ፈርናንዴዝ በሊጉ ለ19ኛ ጊዜ ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።
ጨዋታውን ተከትሎ የ34ኛ ሳምንት ተጠናቋል።
የ35ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከሚያዚያ 23 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳል።