ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድሩ ዝግጅቱን ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2018 (ኢዜአ)፡- 16ኛው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ከሚያዚያ 17 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

 

በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ሞሮኮ፣ቱኒዚያ እና ግብጽ ጋር ተደልድላለች።

በአሜሪካዊው ቤንጃሚን ዚመር የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት ማድረጉን ቀጥሏል።

 

የተሟላ የአሰልጣኞች ቡድን በማደራጀት የምልመላ ሥራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን በተለይም አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ሀገር ቤት ከመጡበት መጋቢት 16 ጀምሮ የሜዳ ላይ፣ የክፍል ውስጥ እና ከተለያዩ ቡድኖች ጋር የሚደረጉ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ያካተተ ጠንካራ ዝግጅት እያደረገ ከአንድ ወር በላይ አስቆጥሯል።

ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ሦስተኛ ሆኖ እንዲጨርስ ያስቻሉ አብዛኞቹ ተጫዋቾች በስብስቡ የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ ቡድኑን የተቀላቀለው አምበሉ ቢንያም አብርሃ ከጉዳት አገግሞ የቡድን ልምምድ እየሰራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም 24 ተጫዋቾች ልምምድ እያከናወኑ ይገኛሉ።

የሴካፋው ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ዳዊት ካሣው፣ የንግድ ባንኮቹ ሁዜይፋ ሻፊ እና ቅዱስ ዳዊት እንዲሁም ወላይታ ድቻዎቹ ቸርነት ኡፋይሳ እና አቤኔዘር ዓለማየሁ በቅርብ ቀናት ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ስብስቡ በካፍ የልህቀት ማዕከት ማረፍያውን በማድረግ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ አዲስ አበባ ስታዲየም፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና አበበ ቢቂላ ስታዲየም በቀን ሁለት ጊዜ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሕዳር ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ መውጣቱን ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ የሚታወስ ነው።

በአፍሪካ ዋንጫው በምድብ ሁለት ኮትዲቯር፣ ካሜሮን፣ ዩጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተደልድለዋል።
 

በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም