የኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ተሸጋግሯል - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ተሸጋግሯል - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ግንኙነት ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ መሸጋገሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ትብብሩ የጋራ መተማመንና ዕድገት በሰነቀ ርዕይ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጿል።
ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሞዛምቢክ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ዳንኤል ፍራንሲስኮ ቻፖ በተገኙበት፤ በወታደራዊ ሥልጠና፣ በከተማ ልማትና በቤት ግንባታ፣ በጤና፣ በሲቪል አቪዬሽን፣ በቱሪዝም እንዲሁም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፤ በተለይም በዲጂታል መታወቂያ እና ዲጂታል የሕዝብ መሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ታሪካዊ የመግባቢያ ሰነዶች መፈረማቸውን ጽሕፈት ቤቱ አመልክቷል።
እነዚህ ስምምነቶች ከፖሊሲ ሰነድነት ባለፈ ለጋራ ብልጽግና ተጨባጭ መንገዶችን የሚቀይሱ መሆናቸውንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ሀገራችን የደረሰችበትን ልምድና እውቀት ለአፍሪካውያን ወንድሞቿ ለማካፈል ያላትን ቁርጠኝነት የምታረጋግጥ ሲሆን፤ በእንዲህ ዓይነት አጋርነቶችም በጋራ ለመማር እና ለማደግ ዝግጁ መሆኗን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።