መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለተፈጥሯዊና ለሰው ሰራሽ ቅርሶች የሚደረግ ጥበቃን በጥናትና ምርምር እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለተፈጥሯዊና ለሰው ሰራሽ ቅርሶች የሚደረግ ጥበቃን በጥናትና ምርምር እያገዘ ነው
ሮቤ፤ ሚያዝያ 19/2018(ኢዜአ)፦ በባሌና ምሥራቅ ባሌ አካባቢ የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ለመጠበቅ በሚከናወኑ ተግባራት በጥናትና ምርምር እያገዘ መሆኑን መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው የድሬ ሼህ ሁሴን መካነ ቅርስን ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መጠበቅና መንከባከብ ዓላማ ያደረገ በትብብር የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ የአካባቢው የቱሪዝም ሀብቶች እንዲለሙና እንዲተዋወቁ በጥናትና ምርምር እያገዘ ነው።
አሁን ላይ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም ቅርሶች በእድሜ በብዛት ለአደጋ እንዳይጋለጡ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም ጥገና ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት አላማ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በባሌ፣ ምሥራቅ ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞን አካባቢ የሚገኙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች እንዲተዋወቁ እገዛ ከማድረግ ባሻገር በቅርሶቹ ላይ የሚደርሱ ተፅዕኖዎች እንዲቀረፉ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
የምርምር ፕሮጄክቱ አባል ሀብታሙ ግዛው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በቅርሶች ላይ የሚደርሱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በጥናት ተለይተው እንዲፈቱ ዓላማ ማድረጉን ተናግረዋል።
በትብብር የሚሰራው ይሄው ፕሮጀክት በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶች ዙሪያ ምርምር በማካሄድ የመፍትሄ አማራጮችን እንደሚሰንድም አመልክተዋል።
የለውጡ መንግስት ትኩረት ከሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ሲሆን በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማስፋት፣ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ እንዲሁም መሰል ተግባራት በስፋትን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።