ቀጥታ፡

በግል ባለሀብት የሚለሙ የግብርና ስራዎች ለኢትዮጵያ የገጠር ሽግግር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የግል ባለሀብቶች በሶላር እና በከርሰ ምድር ውኃ በመጠቀም የሚያለሟቸው የግብርና ሥራዎች ለሀገሪቱ የገጠር ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ዛሬ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሆሞሻ ወረዳ የሚገኘውን ፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ የእርሻ ልማትን በጎበኙበት ወቅት ነው።

በዚህ እርሻ በ250 ሄክታር ላይ 27 ዓይነት የቋሚ ተክል፣ የሰብልና በፍጥነት ደራሽ የፍራፍሬ ልማት በተቀናጀ መልኩ እየተመረተ እንደሚገኝ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።  

ፍቃዱ ነመራ የተቀናጀ የእርሻ ልማት በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የግብርና ሥራ እንዲስፋፋ ለሚደረገው ሥራ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል። 

ይህ በግል ባለሀብት እየለማ ያለው የግብርና ሥራ እንደ ሶላር ያሉ የኃይል አማራጮችን እና የከርሰ ምድር ውኃን በመጠቀም በመስኖ በማልማት ኢትዮጵያ ለጀመረችው የግብርና ልማት እና የገጠር ሽግግር ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የገለጹት።

ከተክል እና የሰብል ልማቱ ጎን ለጎንም የማር ምርት ላይ የሠጠው ትኩረት የአካባቢ እምቅ ፀጋ የመጠቀም ዕይታ በግሉ ዘርፍ እየሠረፀ መሆኑ የታየበት ነው ብለዋል።  

በእርሻው የዶሮ እርባታ፣ የንብ ማነብና የእንስሳት ልማት የተጀመረ ሲሆን የመኖ ዝግጅት መጀመሩም ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም