በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
ሰመራ፤ ሚያዝያ 19/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ለዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል 18 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችና መድሃኒቶችን ዛሬ ድጋፍ አድርጓል።
የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዊቲካ ኖሬ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት ክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን እየተገበረ ነው።
የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገለት የዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት ማዕከልም የዚሁ ትብብር ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቢሮው አዲስ ወደ ስራ ለገባው ማዕከል ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለእናቶችና ህፃናት ጤና መጠበቅ የሚያገለግሉ የህክምና ቁሳቁሶችን እያሟላ መሆኑንም አክለዋል።
የዩኒሴፍ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ተወካይ ዶክተር መሐመድ ኢድሪስ የእናቶችና ህፃናት ጤናን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ድርጅቱ በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ለዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት ማዕከል የተደረገው ድጋፍም የዚሁ ተግባር አካል መሆኑን ጠቅሰው ድጋፍም 18 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
የዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሁሴን ኡመር በበኩላቸው ሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ በቅንጅት እየሰራ ነው።
የዱብቲ አጠቃላይ ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናት ማዕከል ታህሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና በጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።