ቀጥታ፡

ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ ያገኘውን ክህሎት ለእድገት በተግባር መተርጎም ይጠበቅበታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018(ኢዜአ)፦ ትውልዱ በቴክኒክና ሙያ መስክ የሚያገኛቸውን ክህሎቶች በተግባር በመተርጎም ለእድገት የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ።

የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ100ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት "ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ተከብሯል።




በሥነ-ሥርዓቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጁ መምህራንና ተማሪዎች፣ የቀድሞ ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ በኮሌጁ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አውደ-ርዕይ፣ የኪነ-ጥበብ ስራዎችና የባህል አልባሳት ትዕይንት ቀርበዋል።

የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሚደቅሳ ከበደ በዚሁ ወቅት፤ የከተማ አስተዳደሩ የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ብቁ ሙያተኛ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ሰልጣኞች በቂ ክህሎት እንዲጨብጡ ከኢንዱስትሪዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ከቴክኖሎጂ ዕውቀት ውጪ ልማትና ዕድገት ማረጋገጥ እንደማይታሰብ ጠቁመው፤ በዚህ በኩል ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ ይገባል ብለዋል።




የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ተሾመ ፈይሳ በበኩላቸው፤ ባለፉት አሥርት ዓመታት እንጦጦ በሚል ስያሜ ሲጠራ የቆየው ኮሌጅ፤ ዛሬ "ተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ" ተብሎ በይፋ የሚሰየምበት ዕለት በመሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በዓሉን ከማክበር ባለፈ በቴክኒክና ሙያ መስክ የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።




የቀድሞ ተፈሪ መኮንን ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ደጀኔ ተዘራ እንደተናገሩት፤ ማኅበሩ ኮሌጁን ለማጠናከር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ ነው።

የስያሜው መስተካከል ከ100ኛ ዓመት በዓሉ ጋር መገጣጠሙ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።




የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ ኮሌጁ ለሀገር ኩራት የሆኑ በርካታ ሙያተኞችን ማፍራቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የካበተ ልምዱን ለሌሎች የሚያጋራበት ምቹ ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓሉ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ መዝጊያው ሥነ-ሥርዓት ድረስ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋና ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም