ቀጥታ፡

አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው


አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል።

የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አበባ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት በውጤታማነት መረጋገጥ ጀምረዋል።

በግምገማው የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም የተታየ ሲሆን፤ በቀሪ ወራት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የእቅድ አፈጻጸም ውጤታማ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ በአጠቃላይ 96 በመቶ መፈጸም መቻሉን ተናግረዋል።



በዚህም በሁሉም ዘርፎች አዲስ አበባን የኢትዮጵያ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመዲናዋ የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ በተለይም በሰው ተኮር ተግባራት የዜጎችን ሕይወት ከመሠረቱ የቀየሩ በርካታ ፕሮጀክቶች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ከመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በተጨማሪ የምገባ ማዕከላት፣ የተማሪዎች ምገባ፣ የኮሪደር ልማትና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ሕዝብን በማሳተፍ በተከናወኑ ተግባራት የመዲናዋን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ መቻሉንም ነው ከንቲባዋ የገለጹት።

አካባቢንና ወንዞችን ሲበክል የነበረውን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለማሻሻል በተደረገው ጥረት፣ ቀደም ሲል አንድ ብቻ የነበረው የቆሻሻ ማጣሪያ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ 43 ማደጉን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በፍጥነት የመጨረስ ባህል መዳበሩን ጠቅሰው፤ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ከተማ ከማድረግ አኳያ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎች መገንባታቸውንም ተናግረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ከሌብነትና ከብልሹ አሠራር ለመከላከል በተከናወኑ ተግባራት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

የዋጋ ንረትን ከመከላከል አኳያም በከተማዋ የመግቢያ በሮች የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መስፋፋታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም