ቀጥታ፡

የመረጃ ነጻነት ረቂቅ አዋጅ በዕድገት ጉዞ ውስጥ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዲሰፍን ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018(ኢዜአ)፦ የመረጃ ነጻነት ረቂቅ አዋጅ በዕድገት ጉዞ ውስጥ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዲሰፍን እንደሚያስችል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው በመረጃ ነጻነት ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ በዚሁ ወቅት በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ ዋና ዋና ነጥቦችን አብራርተዋል።

የተፈፃሚነት ወሰንን በተመለከተ መንግስት ነክ ስራ ላይ የተሰማራ ወይም መንግስት በንግድ ማህበር ድርሻ ወይም አክሲዮን ያለው ንግድ ማህበር በረቂቅ አዋጁ እንዲሸፈን መደረጉን ጠቅሰዋል።


 

መረጃ የማግኘት መብት የሚገደብባቸው ልዩ ሁኔታዎች ከዓለም አቀፍ ሕጎችና ከአፍሪካ ሞዴል የመረጃ ነጻነት ሕግ ጋር እንዲጣጣሙ ተደርገው በግልጽ መቀመጡንም ተናግረዋል።

ዜጎችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአጭር ጊዜ እና በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችልና የሚያበረታታ የተሳለጠ የመረጃ ተደራሽነት እንዲሰፍን የሚያደርግ ስርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

ከልካይ ያልሆኑ የክፍያ ስርዓት መካተቱንና ለመረጃ ሰጪዎች ህጋዊ ጥበቃ ማድረጉን አብራርተዋል።

የተጠየቀ መረጃ በሚከለከልበት ጊዜ ቀደም ሲል ይወስድ የነበረው ረጅም የይግባኝ ጊዜ በረቂቅ አዋጁ እንዲያጥር ተደርጓል ብለዋል።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአዋጁን አፈጻጸም በአግባቡ መከታተል እንዲችል በቂ ሥልጣንና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው የሚያስችሉ ዝርዝር ድንጋጌዎች ተካተዋል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አዝመራ አንደሞ፤ ማሻሻያው በመንግስት፣ በዜጎች እና በባለድርሻ አካላት መካከል በሚከናወነው የዕደገት ጉዞ ውስጥ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት እንዲሰፍን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ረቂቅ አዋጅ የተደራጀና ጠንካራ አሰራርን በመዘርጋት ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና ተጠያቂነት እንዲሰፍን የሚያስችሉ የተሟሉ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በሰጡት ማጠቃለያ፤ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገው ካለው ወቅታዊ ለውጥ እና አዳዲስ ሁኔታዎች አኳያ ተገቢ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበሩ መሠረታዊ ጉዳዮችን በአግባቡ መለየት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በተለይም በትርጓሜ አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በተጨማሪም የማሻሻያ ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን ማየትና መቅሰም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም