ቀጥታ፡

አፍሪካውያን የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ አብዮትና ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የማዕድን ሀብታቸውን እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ ማቅረብ አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦‎ አፍሪካውያን የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ አብዮትና ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የማዕድን ሀብታቸው ላይ እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከታንዛኒያ የአፍሪካ ዘላቂ ልማት አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የአፍሪካ ወሳኝ ማዕድናትን ለአረንጓዴ የኢንዱስትሪ አብዮትና ዘላቂ ልማት ማዋል" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁት የ12ኛው የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ቅድመ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካ እንደ ኮባልት፣ ሊቲየም፣ ግራናይት እና ሌሎች የከርሰ ምድር ሀብቶችን ጨምሮ የዓለምን 30 በመቶ ማዕድናትን ይዛለች፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብቻዋን የዓለምን ከፍተኛ የኮባልት ማዕድን የያዘች መሆኑን ገልጸው፤ ይሄውም አፍሪካን የዓለም አቀፍ የኃይል ሽግግር /Energy Transition/ ማዕከል ያደርጋታል ብለዋል፡፡

አፍሪካ ዩራኒዬምና ሌሎች የከርሰ ምድር የከበሩ ማዕድናት ባለቤት መሆኗን በመጥቀስ፤ ለዓለም አቀፉ የኒውክሌር ኃይል አቅርቦት አስተዋጽኦ ከማድረግ ባለፈ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ኒውክሌር ኃይል ልማት እያመሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ የከበሩ ማዕድናት ባለቤት ብትሆንም አብዛኛው በጥሬ እቃ መልክ ወደ ውጭ የሚላክ በመሆኑ የአህጉሪቱ የእርስ በእርስ ግብይት ከሁለት በመቶ እንዳማይዘል ተናግረዋል፡፡

በአህጉሪቱ የማዕድናት ማምረቻና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን መገንባት ቢቻል በየዓመቱ ከ24 ቢሊየን ዶላር በላይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘትና ለ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ የማዕድን ፖሊሲ ለእሴት መጨመር፣ ኢንዱስትሪ ልማትና ሁሉን አቀፍ ልማት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በአህጉሪቱ የተቀናጀ ቀጣናዊ ኢንዱስትሪ ለመገንባት ያለውን ፍላጎት በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ አህጉራዊ የማዕድን ሀብቶችን ወደ ዘላቂ ብልጽግና መለወጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቀጣናዊ እሴት ሰንሰለትን በማጠናከር የማዕድን ጸጋዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ጥረት ትብብሩን ማጠናከሩን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የአፍሪካ ዘላቂ ልማት አመራር ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካዳሪ ሲንጎ በአፍሪካ ሁሉን አቀፍና አካታች ዕድገት ለማስመዝገብ የማዕድን ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አፍሪካውያን በተፈጥሮ ሀብታችን ላይ የሚኖረን ትብብርና ተሳትፎ ስትራቴጂያዊና መዳረሻ ግብ ያለው መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ አብዮት ሽግግርን ለመፈጠር በአቅም ግንባታ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም