ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ጥምር ኮሚቴ በማቋቋም በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በሞዛምቢክ የመከላከያ ሚኒስትር በኢ-ክርስቲያቮ አርቱር ቹሜ የተመራውን ሉዑካን ቡድን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።


 

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጣር በ2009 በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገውን ወታደራዊ ግንኙነት መሰረት በማድረግም የጋራ ጥምር ኮሜቴ በማቋቋም ወደ ስራ መግባት በሚቻልባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በጋራ መስራት የበለጠ አቅም ለማግኘት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ላይ ውጤት ለማምጣት እንደሚጠቅም በመድረኩ ላይ የተነሳ ሲሆን የዛሬው ውይይትም ጥምር ኮሚቴውን ለማቋቋምም ሆነ የወደፊቱን ወታደራዊ ግንኙነት እና ትብብር ለማስቀጠል የራሱን ሚና ይጫወታል መባሉን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም