የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር የአሕጉሪቱን የማዕድን ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር የአሕጉሪቱን የማዕድን ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በተሟላ ሁኔታ በመተግበር አሕጉሪቱ ያላትን ዕምቅ የማዕድን ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ትብብር መፍጠር እንደሚገባ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ፡፡
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከታንዛኒያ የአፍሪካ ዘላቂ ልማት አመራር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የአፍሪካ ወሳኝ ማዕድናትን ለአረንጓዴ የኢንዱስትሪ አብዮትና ዘላቂ ልማት ማዋል" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጁት የ12ኛውን የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ፎረም ቅድመ ጉባኤ አካሂዷል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካ ዕምቅ የማዕድን ሃብት የአህጉሪቱ ብልፅግና የማፋጠን ግዙፍ አቅም አለው።
የአህጉሪቱን ሃብት በጥሬ ዕቃ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ዕሴት የታከለበት ማዕድን ማምረት የሚያስችል ኢንዱስትሪ መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የመገበያያ ገንዘብ የነበሩ እንደኮባልት፣ ሊቲየም፣ መዳብ፣ ማንጋኒዝና ብርቅዬ የከርሰ ምድር ማዕድናት የታደለች መሆኗን ተናግረዋል።
ማዕድናቱ በዓለም የግብይት ሰንሰለት ላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸውና ለባትሪ፣ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪና ታዳሽ ኃይል ልማት የሚያገለግሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዚህም የአፍሪካን የአረንጓዴ ሽግግር በማጠናከርና የከበሩ ማዕድናትን በማልማት የአህጉሪቱን ዕምቅ የተፈጥሮ ፀጋና የድኅነት ተቃርኖ ማስታረቅ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
የአህጉሪቱን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ትስስር የሚያሳልጥ መሰረተ ልማት ግንባታን በማጠናከር የኃይል ትስስርና የሎጀስቲክስ አቅም መገንባት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በተሟላ መንገድ በመተግበር የተቀናጀ አህጉራዊ የዕሴት ሰንሰለትን የሚያፋጥን የትብብር ሥርዓት መፍጠር ይገባል ብለዋል።
የአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ደንብና ደረጃዎችን በማጣጣም በዓለም አቀፍ የገበያ ሥርዓት የመደራደር አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይም የአንድ አፍሪካ ሀገር የማዕድን ሃብት ተቆፍሮ፣ በሌላ የአፍሪካ ሀገር የሚቀነባበርበትንና በሶስተኛ የአህጉሪቱ ሀገር ምርት ሆኖ የሚወጣበትን ሁኔታ ጭምር ማሰብ እንደሚጠይቅም አብራርተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በዕርስ ትብብር የዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ኃይል የሚሆኑበትን አቅም በመገንባት ተጠያቂነት የሰፈነበት የማዕድን ልማትና ተቋማትን መገንባት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
አፍሪካ ፍትሕዊ ዓለም አቀፍ አጋር እንጂ ምፅዋት የምትሻ አህጉር አለመሆኗን ጠቁመው፤ የልማት አጋሮችም አህጉሪቱን ከጥሬ ዕቃ ምንጭነት ባሻገር የስትራቴጂክ ኢንዱስትሪ መዳረሻ በማድረግ ሊመለከቷት ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ዘላቂ ልማት ቀጣናዊ ጉባኤም የአየር ንብረት ለውጥ፣ ዝቅተኛ የካርቦን ሽግግርና የማዕድን ሃብት ልማትን የሚያፋጥን አህጉራዊ ትብብርን ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አንስተዋል።
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA