ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የሰሜን ኮሪያ አምባሳደር ሲም ቶንግ ጎክ አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የሰሜን ኮሪያ አምባሳደር ሲም ቶንግ ጎክ አሰናበቱ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የሰሜን ኮሪያ አምባሳደር ሲም ቶንግ ጎክን አሰናብተዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፤ አምባሳደር ሲም ቶንግ ጎክ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እንዲጠናከር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያና ሰሜን ኮሪያ መካከል በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ታሪካዊ ወዳጅነት መኖሩንም ገልጸዋል።
የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በማሳደግ የጋራ ተጠቃሚነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ የሀገራቱን የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ወዳጅነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በመልዕክታቸው አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ላበረከቱት ሁሉ ምስጋናቸውን ገልፀው፤ ለወደፊቱ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።