ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጉዞዋ ወደ ተጨባጭ ምዕራፍ ተሸጋግሯል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጉዞ ወደ ተጨባጭ ምዕራፍ መሸጋገሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የዓለም ንግድ ድርጅት ሰባተኛው የኢትዮጵያ የስራ ቡድን ስብሰባ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድል የተመዘገበበት መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድር ሂደትና በተከናወኑ ስራዎች ላይ እንዲሁም በጄኔቫ የተካሄደውን የዓለም የንግድ ድርጅት ሰባተኛው የኢትዮጵያ የስራ ቡድን ስብሰባ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ከፍተኛ ስራ መስራቷን ገልጸው፤ እነዚህ ስራዎች በእውቀት እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መንገድ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለማድረግና ድርድሩ ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ውጤታማ ድርድሮች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዓለም አቀፍ የንግድ አባልነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው ከአባል ሀገራት ለሚቀረቡ ጥያቄዎችም የሀገርን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ምላሽ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በጄኔቫ የተካሄደው የዓለም የንግድ ድርጅት ሰባተኛው የኢትዮጵያ የስራ ቡድን ስብሰባ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድል የተመዘገበበት መሆኑን እንዲሁም መግባባት ላይ የተደረሰበትና የሚቀርቡ ጥያቄዎችም እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጉዞ ግልጽ ወደሆነ ምዕራፍ መሸጋገሩን ጠቁመው በድርድር ሂደቱ ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸው ስራዎች በአባላቱ እውቅና እንደተሰጠውም አንስተዋል።

የዓለም የንግድ ድርጅት ስምንተኛው የኢትዮጵያ የስራ ቡድን ስብሰባ በመጪው መስከረም ወር እንደሚካሄድ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም