በዞኑ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ተከናውነዋል
ጎንደር ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በማእከላዊ ጎንደር ዞን በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማሕበረሰቡ ባደረገው ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህብረተሰቡን በንቅናቄ በማሳተፍ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ተሰርቷል።
በዚህም ከ400 በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃት ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም 18 ቤተ መጻህፍት፣ 923 መጸዳጃ ቤቶችና 1 ሺህ 300 የመጠጥ ውሃ ተቋማት በማስገንባት ተማሪዎች የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በተለይም 222 የመምህራን መኖሪያ ቤቶችን በማስገንባት ተረጋግተው የመማር ማስተማር ስራውን ለማቀላጠፍ እንዲችሉ መደረጉንም አስረድተዋል።
የአማራ ልማት ማህበርም ስድስት የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ማስጀመሩን ነው የጠቆሙት።
የትምህርት ሚኒስቴርም እንዲሁ 15 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማስጀመር የተቋራጭ ልየታ እያካሔደ መሆኑን አብራርተዋል።
በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችም በቆላድባ፣ በጭልጋና በወገራ ወረዳዎች ሶስት ትምህርት ቤቶችን እያስገነቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና የመምህራን መጠለያዎች በህብረተሰቡ ድጋፍ መሰራታቸውን የተናገሩት በወገራ ወረዳ የኮሶዬ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሰጠኝ ታከለ ናቸው፡፡
በምእራብ ደንቢያ ወረዳ የጯሂት ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፉ ባዩ በበኩላቸው፤ በንቅናቄው ህብረተሰቡ የሚያደርገው ድጋፍ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እያገዘ ነው ብለዋል፡፡