ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ማዕከል ያደረገ ውጤታማ የልማት አቅጣጫ ላይ ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ማዕከል ያደረገ ውጤታማ የልማት አቅጣጫ ላይ ናት
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ማዕከል ያደረገ ውጤታማ የልማት አቅጣጫ ላይ ናት ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የአየር ንብረት ኢንቨስትመንት ፈንድስ(CIf) ከኢትዮጵያ መንግሥት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የልምድ ልውውጥ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ ምሁራን፣የልማት አጋሮችና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ አምባሳደሮችና የሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ላይ የተለያዩ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ያገኟቸው ውጤቶች ላይ ተሞክሮዎችን አቅርበው የልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የዕድገት ራዕይና አቅጣጫ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ማዕከል ያደረገ ነው።
ለዚህም ታዳሽ ሃይልን ማስፋፋት፣የውሃ አቅርቦት ማሻሻል፣ የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ የማህበረሰቡን የመቋቋም አቅም የሚያሳድጉ ውጤታማ ተግባራት መከናወኑን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ የኮርደር ልማትና የወንዝ ዳር ልማት ስራዎች ከተማዋን ዘመናዊ ከማድረጋቸውም ባሻገር እድገት ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተናበበ መልኩ እንዴት እንደሚከወን ማሳያ ነው ብለዋል።
መንግሥትም ከአየር ንብረት ለውጥ ኢንቨስትመንት ፈንድስ ጋር በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ በአማራጭ ሃይል አቅርቦቶች እና ተፈጥሮን መሰረት ያደረጉ መፍትሔዎች ላይ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑንም አመልክተዋል።
የዛሬው የልምድ ልውውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ዙሪያ ያላትን ተሞክሮ ለማካፈል፤ ከሌሎች ተሳታፊዎችም ለመማር ዝግጁ ናት ሲሉም ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ኢንቨስትመንት ፈንድስ(CIF) ዋና ስራ አስፈጻሚ ታሪዬ ባድጌሲን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በአረንጓዴ አሻራ አርዓያ የሚሆን ተግባር መፈጸሟን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከዚህ ቀደም ስኬታማ በሆነ መንገድ ማስተናገዷም በዘርፉ ያላትን የላቀ ተሞክሮ ያሳያል ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጋራ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።