በአማራ ክልል ከ22 ሚሊዮን በላይ የቡናና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ22 ሚሊዮን በላይ የቡናና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል
ባህርዳር፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ22 ሚሊዮን በላይ የቡናና የሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለጸ።
በቢሮው የሆርቲካልቸር ባለሙያ አቶ አወቀ ዘላለም ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በክልሉ ተስማሚ ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ያላቸውን አካባቢዎች በመለየት ቡናና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በክላስተር የማልማት ስራ እየተካሄደ ነው።
በተያዘው በጋ ወቅትም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና በሽታን የሚቋቋሙ ከ22 ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የቡናና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ወደ 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጋው የቡና ችግኝ ሲሆን ቀሪው ደግሞ የቆላና የደጋ ፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ክልሉን በቡናና ፍራፍሬ ልማት ሞዴል ለማድረግም ሽፋኑንና ምርታማነቱን በማሳደግ ላይ በማተኮር የአርሶ አደሩ ዘላቂ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለመጪው ክረምት ለተከላ እየተዘጋጀ ያለው ችግኝም ከ32 ሺህ ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የሚተከል መሆኑን አስረድተዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠህናን ወረዳ አርሶ አደር ተፈራ መለሰ ፤ ባለፉት ዓመታት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ቡናን የማልማት ስራ መስራታቸውን ጠቅሰዋል።
በመጪው የክረምት ወቅትም በተጨማሪ ሩብ ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝን በኩታ ገጠም ለመትከል አቅደው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከል የተሻለ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለፁት ደግሞ የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ውበት ተስፌ ናቸው።
ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከሉ ወደ 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚጠጋ ቁጥር ያላቸው የቡና፣ የቆላና ደጋ ፍራፍሬ ችግኞች 93 ነጥብ 5 በመቶው መጽደቁን የቢሮው መረጃ ያመለክታል፡፡