ቀጥታ፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሁሉም ተቋማት ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦የሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሁሉም ተቋማት ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት እየተገነባ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።

ሹመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ላሳዩት አመራርና ኢትዮጵያ በአህጉሪቷ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ላለው የላቀ ሚና የተሰጠ እውቅና ነው።


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እንደገለጸው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ሥነ ምግባራዊ መርሆች በተከተለ መልኩ በማልማት፣በመመራመር እንዲሁም ተግባራዊ በማድረግ በኩል ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆን ለተሰሩ ስራዎች እውቅና የሰጠ ነው።

በኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ጨምሮ በዘርፉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።ለዚህ ስኬትም የተለያዩ ተቋማት በቅንጅት በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ሀገርን በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬትና ለዲጂታል ኢትዮጵያ-2030 ዕቅድ አዳዲስ የፈጠራ ዕሳቤዎችን በማፍለቅ ጉልህና ገንቢ ሚና እየተወጣ ነው።


 

የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በለጠ እሱባለው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለአመራር ልህቀትና ቴክኖሎጂ ልማት አስገዳጅ እየሆነ መጥቷል።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርኩም የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሠረተ ልማት በማስፋፋት በኢትዮጵያ አስቻይ የዲጂታል ከባቢ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የፋይበር፣ ፓወርና ሌሎች የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓትን የሚያዘምን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስም በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በዲጂታል ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃይል ማፍራት እየተቻለ መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ዲጂታልና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ የቦርድ ሊቀ መንበርና የአፍሪካ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ባህሩ ዘይኑ፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል መሠረተ ልማት ወሳኝ ሽግግር እያደረገች ነው ብለዋል።


 

ለአብነትም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓለም አቀፍ ተፅዕኖን በመገንዘብ ኢንስቲትዩት በማቋቋምና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ የመክፈት ዝግጅት መኖሩ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።

የግሉ ዘርፍም የዲጂታል ልማት አስቻይ የፖሊሲ ማዕቀፎችን በመጠቀም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን የሚያሳልጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት መተግበሪያን ማልማት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ዲጂታልና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚም የኢትዮጵያን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ዲጂታልና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ ተባባሪ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ሸጋው አናጋው፤ የተቋማትን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ትግበራ ለማፋጠን የስልጠና አቅም ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲም በዘርፉ በዕውቀትና ክህሎት የበለጸጉ ዜጎችን በማፍራት ሁሉንም ተቋማት ብቁ የዲጂታል መሠረተ ልማት ለማስታጠቅ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የሁሉንም ተቋማት የዳታ ሥርዓት የማሰባሰብና መተንተን አቅም ለማጎልበት የመንግስትና የግል ተቋማት ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በቀጣይም በኢትዮጵያ የስታርት አፕ ፖሊሲ ማዕቀፍ በዳታ ሳይንስ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎትና በሮቦቲክስ ዘርፍ ብቁ ወጣቶችን ለማፍራት የግሉን ዘርፍ አቅም ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም