ዩኒቨርሲቲው ዕውቀትና ክህሎት ያለው ተወዳዳሪ የሰው ኃይል የማፍራቱን ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ዕውቀትና ክህሎት ያለው ተወዳዳሪ የሰው ኃይል የማፍራቱን ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል
አሰላ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በዕውቀትና በክህሎት የበቃ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ተግባር ተኮር የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ ባቲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተቋሙ የሚሰጣቸው የትምህርት ፕሮግራሞች የጥራት ዕውቅና ያላቸውና የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ እንዲሆኑ እየተሰራ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በ5 ኮሌጆችና በአንድ ትምህርት ቤት ይሰጡ የነበሩ ንድፈ-ሀሳብ (Theory) ላይ ያተኮሩ የመማር ማስተማር ሂደቶችን ወደ ተግባር ተኮር (Applied) የመቀየር ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ሙስጠፋ ገልጸዋል።
ይህ አሰራር የመማር ማስተማር ሂደቱን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የጥራት ዕውቅና ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
በዚህም የአዋላጅ ነርስ፣ የፋርማሲና የሜዲሲን ትምህርት ክፍሎች የጥራት ዕውቅና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም 5 የህክምና እና 3 የግብርና ፕሮግራሞች የጥራት ዕውቅና እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው እ.ኤ.አ በ2030 ከምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ የ"አፕላይድ" ዩኒቨርሲቲ አንዱ ለመሆን ግብ ማስቀመጡን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በአካዳሚክ ዘርፍ ብቻ ከ15 በላይ የመማር ማስተማር መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።
28 የተለያዩ ላቦራቶሪዎችን በዘመናዊ ቁሳቁስ የማደራጀትና ተጨማሪ ቤተ-ሙከራዎችን የመገንባት ስራ እየተከናወነ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በግብርና፣ በጤና፣ በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታና ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅርቡ በተሰጠው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና የጤና ዘርፍ (አዋላጅ ነርስ፣ ፋርማሲና ሜዲሲን) ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ማለፋቸው የትምህርት ጥራቱን ለማረጋገጥ እየተሰራ ላለው ስራ ማሳያ መሆኑም ተጠቅሷል።
ዩኒቨርሲቲው በ2019 ዓ.ም በአዲሱ ፍኖተ-ካርታ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስርን በማጠናከር የገበያ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የሰው ኃይል ልማት ላይ በትብብር ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ተመላክቷል።