ቀጥታ፡

ማንችስተር ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በማንችስተር ዩናይትድ እና በብሬንትፎርድ መካከል ዛሬ ይደረጋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይካሄዳል።

ማንችስተር ዩናይትድ በ58 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ብሬንትፎርድ በ48 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ10ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ ብሬንንትፎርድ በሶስቱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው ሁለቱም በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

ብሬንትፎርድ ከዩናይትድ ጋር ያደረጋቸውን ያለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አሸንፏል። 

በ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቼልሲን 1 ለ 0 ያሸነፈው ማንችስተር ዩናይትድ ተከታታይ ድሉን ካስመዘገበ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመሳተፍ እድሉ የበለጠ ሰፊ ይሆናል።

ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አቻ የወጣው ብሬንትፎርድ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና የአውሮፓ መድረክ ተሳትፎውን ለማረጋገጥ ይጫወታል።

የ40 ዓመቱ ክሪስ ካቫናግ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም