ቀጥታ፡

በዞኑ በሻይ ቅጠል ልማት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል

ጅማ  ፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦በጅማ ዞን የሻይ ቅጠል ልማትን በኢኒሼቲቭ መልክ በመተግበር የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ ለበርካቶች የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑ ተመለከተ።

በዞኑ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሻይ ቅጠል የማልማት ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት ገልጿል።

የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ቲጃኒ ተማም እንዳሉት፤  በዘንድሮ ክረምት በተመረጡ ስድስት ወረዳዎች  የሚተከል 50 ሚሊየን የሻይ ቅጠል ችግኝ እየተዘጋጀ ነው።


 

የችግኝ ተከላውን በህዝብ ተሳትፎ በማከናወን 1ሺህ 725 ሄክታር መሬት ለመሸፈን ከወዲሁ ወደ ስራ መገባቱን  አስረድተዋል። 

የሻይ ቅጠል ልማቱን ከማስፋፋት ባለፈ የገበያ ትስስር የመፍጠርና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለፋብሪካ ለማቅረብ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በዞኑ በሻይ ቅጠል ልማት ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት በሚያደርግላቸው የሙያና የተሻሻሉ ዝርያዎች ድጋፍ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደገው ተናግረዋል።


 

በዞኑ ሻይ ልማት ላይ ከተሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ነዋሪው ስራጅ ሼክ ከድር ፤ በሻይ ቅጠል ልማት ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ሁለት አመታት ወዲህ ገቢያቸው መጨመሩን ተናግረዋል። 


 

ወረዳው የሰጣቸውን ምርታማነታቸው የተሻሻለ የሻይ ተክልን በማልማትና የባለሙያ ድጋፍን በማግኘታቸው ተጠቃሚነታቸው እንዳደገ ጠቁመዋል። 

ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር  ሱልጣን አባሞጋ፤ ከዚህ ቀደም ተሰማርተውበት በነበረው የተለያዩ የሰብል ልማቶች ተጠቃሚነታቸው አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በሻይ ቅጠል ልማት ተሰማርተው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ጠቁመው ለስራቸው ስኬታማነት ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል በግብርና ፅህፈት ቤት ባለሙያዎች እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም