ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ነዳጅን ጨምሮ ህገ ወጥ ንግድን የመከላከልና የመቆጣጠር  ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ሐረር፤ ሚያዝያ 19/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን ጨምሮ ህገ ወጥ ንግድን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለጸ።

የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ተከትሎ የተከሰተው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ግብይት መስተጓጎል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳያስከትል መንግስት መመሪያዎችና አሰራሮች መዘርጋቱ ይታወሳል። 

የሐረሪ ክልል ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዳስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩስፍ እንዳሉት፤ በክልሉ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን ጨምሮ ህገ ወጥ ንግድን የመከላከልና የመቆጣጠር  ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ ይገኛል።

በተለይም ያለ ንግድ ፈቃድ ግብይት የሚፈጽሙ፣ ምርት የሚሸሽጉና በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በየወረዳው የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም በክልሉ በህገ ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ነጋዴዎችን አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ  ወደ ህጋዊነት የማምጣት ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

ከነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ጋር በተያያዘም በክልሉ እየቀረበ የሚገኘውን ነዳጅ በቁጠባና ትኩረት በሚሹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መሰረት ባደረጉ መልኩ የማሰራጨት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይም በክልሉ ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ከመከላከል አንጻር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ፈጽመው በተገኙ አራት የነዳጅ ማደያዎችና ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ ሁለቱ የነዳጅ ማደያዎች ለስድስት ወራት እንዲታገዱ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ የነዳጅ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ አግባብነት እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የክትትል፣ የቁጥጥርና የተጠያቂነት ስራዎች በተቀናጀ መልኩ እየተካሄዱ መሆኑን አቶ ኡስማኢል አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም