የመገናኛ ብዙኃን ሚና በምርጫ ወቅት - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙኃን ሚና በምርጫ ወቅት
በኢዜአ ዐይን…!
በዮሐንስ ደርበው
የመገናኛ ብዙኃን ሚና በምርጫ ወቅት
በአንድ ሀገር ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት መጎናጸፊያ፤ለሀገራዊ መግባባትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።በሀገራችን ለ7ኛ ጊዜ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫም የፊታችን ግንቦት 24 ጊዜ ተቆርጧል።ከዚህ ጋር ተያይዞም በምርጫ ሰሞን መገናኛ ብዙኃን የጎላ ሚና አላቸው ተብሎ ይጠበቃል።በዚህ ፅሁፍም ይህን ሚናቸውን እንቃኛለን።
• መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ወቅት አዘጋገብ ምን ይጠበቅባቸዋል?
በምርጫ ወቅት መገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃ ለሕብረተሰቡ በማድረስ ለሂደቱ ስኬታማነት፣ ተዓማኒነትና ተቀባይነት የማይተካ ሚና አላቸው።መገናኛ ብዙኃን ብሎም ጋዜጠኞች ሚናቸውን በአግባቡ ለመወጣት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታን እና ዓለም አቀፋዊ ለውጦችን (ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ) ጉዳዮችን በውል ማጤን አለባቸው።
መገናኛ ብዙኃን ገለልተኛ ሆነው ያዩትን፣የታዘቡትን ሙያዊ ሥነ-ምግባር በመከተል ለሕዝቡ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ይጠበቃል።በዚህ ሂደትም በጥብቅ ኃላፊነት ተግባራቸውን የማከናወን ግዴታ አለባቸው።
በምርጫ ዘገባ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ትኩረትና ሚናም፤ ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ አስፈላጊውን መረጃ ለሕዝቡ ማሻገር ነው።
መገናኛ ብዙኃን ሲባልም፤በየጊዜው የሚወጣ ኅትመትን፣ የብሮድካስት አገልግሎትን እና የበይነመረብ መገናኛ ዐውታርን በመጠቀም መረጃዎቻቸውን ለሕዝብ ለማቅረብ የተቋቋሙ አካላት ማለት ነው።
በምርጫ ወቅት የምርጫ ሂደትን ለመዘገብ (ለመከታተል) ዕውቅና (ፈቃድ) የተሰጠው የመገናኛ ብዙኃን (ጋዜጠኛ) ግዴታዎች እንዳሉበትም መገንዘብ ይገባል። ከእነዚህም መካከል፡-
• የሕዝብን ሰብዓዊ መብትና መሠረታዊ ነጻነቶች ማክበር፤
• የምርጫ ቦርድን፣የምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት አካላትን ሚና እና ሥልጣን ማክበር፤
• ለምርጫ አስፈጻሚዎች ስለ ኃላፊነታቸው ምክር ወይም መመሪያ አለመስጠት፤
• መራጩ ድምፁን ለማን እንደሰጠ አለመጠየቅ፤
• የሕግ ጉዳዮችን በራስ አለመተርጐም እና የምርጫ ሂደትን የሚመለከት ሕጋዊ ያልሆነ መረጃ ወይም መመሪያ አለማስተላለፍ፤
• መራጭ በምሥጢር ድምፅ በሚሰጥበት ክፍል ወይም ለድምፅ መስጫ የተከለለ ቦታ ካሜራም ሆነ ሌላ የድምፅ ወይም የምስል መቅረጫ መሣሪያ አለመጠቀም፤
• ከአድልዎና ከወገንተኝነት በፀዳ ሁኔታ ተግባራትን ማከናወን፤
• የሀገሪቱን እና የአካባቢውን ባሕልና ልምድ ማክበር፤
• በቦርዱ የተሰጠውን የመታወቂያ ካርድ በሚታይ መልኩ በመያዝ መንቀሳቀስ፤
• የመራጭ ምዝገባ መረጃዎች በሠነድ ላይ ሲሰፍሩ ወይም መራጩ በድምፅ መስጫው ወረቀት ላይ የምርጫ ምልክት ሲያደርግ በፊልም አለመቅረፅ፤ፎቶግራፍም አለማንሳት፤
• የመራጮች ማንነትን ግላዊነት በሚነካ ሁኔታ የመራጮችን መዝገብ፣ የመራጮችን ምዝገባ መታወቂያ ወይም ማንኛውንም ተመሳሳይ ሠነድ በፊልም አለመቅረጽ፣ ፎቶግራፍ አለማንሳት ወይም ኮፒ አለማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
በምርጫ ዘገባ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ትኩረትና ሚናም፤ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ አስፈላጊውን መረጃ ለሕዝቡ ማድረስ ሲሆን፤ ለአብነትም እንዲያተኩሩባቸው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል ቀጥሎ የተጠቀሱት ይገኙበታል፡-
• ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ማቅረብ፡-መገናኛ ብዙኃን ማንኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ከመደገፍ ወይም ከማጥላላት ተቆጥበው ገለልተኛና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝቡ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
• ለመራጮች ትምህርት (ወቅታዊ መረጃዎችን) መስጠት፡- ስለ ምርጫው ሂደት ዝርዝር ጉዳዮች ሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ከመገናኛ ብዙኃን ይጠበቃል። በዚህም መሠረት ለአብነት፤ ስለ መራጮች ምዝገባ ሂደት (መቼ እንደሚጀመር፣ መቼ እንደሚጠናቀቅ፣ ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ እና ስለ ድምጽ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ለሕዝቡ ግንዛቤ መፍጠር) ዋነኛው ተግባራቸው ነው።
• የሰላምና የአንድነት ግንባታ፡- በምርጫ ወቅት የሚነሱ ግጭቶችን ከማባባስ ይልቅ ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን የሚያጠናክሩ ዘገባዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ውይይቶችንና ክርክሮችን በማመቻቸት ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ምቹ መድረክ መፍጠርም አንዱ ሚናቸው ነው።
• የሥነ-ምግባር ደንቦችን ማክበር፡- ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት ከማንኛውም አካል የሚመጣባቸውን ጫና በመቋቋም፤ የጥቅም ግጭቶችን በማስወገድና ከጥላቻ ንግግሮች በመራቅ በሙያዊ ሥነ-ምግባር መመራት ይኖርባቸዋል።
በአጠቃላይ መገናኛ ብዙኃን፤ ሕብረተሰቡ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲሰጥ የማገዝ፣ ለፓርቲዎች የሐሳብ መድረክ የመፍጠር፣ መራጩን ሕዝብ የማሳወቅ (ማስተማር)፣ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃ የማሠራጨት እንዲሁም ለቅድመ ምርጫ፣ ለምርጫ ወቅት እና ድኅረ ምርጫ ሰፊ ሽፋን እንዲሰጡ ይጠበቃል።
በምርጫ ዘገባ መርሆዎች (ገለልተኝነት፣ ሚዛናዊነት፣ ትክክለኛነት፣ ፍትሐዊነት፣ ኃላፊነት) መሥራትም እንዲሁ።
ጋዜጠኞችም፤ የዘገባ መርሆዎችን ማክበር፣ የተለያዩ ፓርቲዎችን ሐሳብ ማስተናገድ፣ ግልጽና የማያሻማ ቋንቋ መጠቀም፣ ፖሊሲና ማኒፌስቶ ላይ ማተኮር፣ አሳታፊና አካታች መሆን አለባቸው።
በዚህ ሥራም የመረጃ ምንጮቻቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት ሊሆኑ ይገባል።
በአጠቃላይ መገናኛ ብዙኃን ለሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ስኬታማነት የምርጫ ሕጉንና የመገናኛ ብዙኃን ዐዋጅን በተከተለ መልኩ በመዘገብ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የዐቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታውቋል።
መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ወቅት ሙያዊ ሥነ-ምግባርን የተከተለ አሳታፊና አካታች የሆነ ዘገባ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝቧል፡፡