ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በከተሞች የቱሪዝም እንቅሰቃሴን የሚያነቃቁ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዳማ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በከተሞች የቱሪዝም እንቅስቃሴን የሚያነቃቁ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ።

በአዳማ ከተማ የተገነቡ የልማት ሥራዎች እና የቱሪዝም መስኅቦችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ከተማ አሥተዳደሩ ከኢትዮጵያ ሞተርስ አሶሴሽን ጋር በመተባበር የመኪና ውድድር አካሂዷል።


 

የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ በዚሁ ወቅት፤ የክልሉ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በክልሉ በከተሞች የቱሪዝም እንቅስቃሴን የሚያነቃቁና የሚያጠናክሩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በተለይ በከተሞች እየተካሄዱ ያሉ የኮሪደር ልማቶች ከተሞች እንዲነቃቁ እና የቱሪስት እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ምቹ መደላድል እየፈጠሩ ነው ብለዋል።

ቱሪዝም የሀገር ገጽታን ለመገንባት ያለው ድርሻ የላቀ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ይህንን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ በመላ ክልሉ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ከሚገኙ ከተሞች  አዳማ አንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ ዛሬ ያስተናገደችው የመኪና ውድድር የከተማዋን የቱሪዝም ሀብት በማስተዋወቅና በማጠናከር  ረገድ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አውስተዋል።

የመኪና ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሪቱንና ከተሞችን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ጠቁመው ወደፊት በቋሚነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።


 

የአዳማ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው፤ አሥተዳደሩ ከተማዋን የቱሪዝም፣ የኮንፈረስንስ፣ ቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ መሠራቱን ገልጸዋል።

በዚህም አበረታች ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው በተለይ የቱሪስት ፍሰትን ለማሳለጥ በስፋት መሠራቱን አረጋግጠዋል።

በከተማዋ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ምቹ እና ደኅንነታቸው የተጠበቀ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

ከለውጡ ወዲህ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ለኢኮኖሚ፣ ለቱሪዝምና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም አንስተዋል።

ከልማት ፕሮጀክቶች መካከልም የከተማዋን እድገት በሚመጥንና ለቱሪዝም ልማት በሚያግዝ አግባብ የኮሪደር ልማት በተሟላ መልኩ መሠራቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በከተማዋ የተገነቡ የልማት ሥራዎች እና የቱሪዝም መስኅቦችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ  አሥተዳደሩ ከኢትዮጵያ ሞተርስ አሶሴሽን ጋር በመተባበር የመኪና ውድድር ማካሄዱን አስታውቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ሞተርስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አዲስ ዓለማየሁ በበኩላቸውበዛሬው የመኪና ውድድር 1 ሺህ እስከ 2 ሺህ ሲሲ ጉልበት ያላቸው 20 በላይ መኪናዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በውድድሩም አራት የውጪ ሀገራት ዜጎች መሳተፋቸውንና የውድድሩ ድምቀት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በአምስት ምድብ ተሳትፈው 1 እስከ 3 ለወጡ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት መበርከቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ውድድሩን በበላይነት ላጠናቀቁ የሜዳሊያ ሽልማት እንዲሁም ለውድድሩ ስኬታማነት አስተዋጾ ላደረጉ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም