የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የልምምድ ቦታ እጥረትን በዘላቂነት ቀርፈውልናል - አትሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የልምምድ ቦታ እጥረትን በዘላቂነት ቀርፈውልናል - አትሌቶች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የተገነቡ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለዓመታት ይቸገሩበት የነበረውን የልምምድ ቦታ እጥረት በዘላቂነት እንደቀረፉላቸው አትሌቶች ገለጹ፡፡
መንግሥት ከለውጡ ወዲህ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እና የልምምድ ቦታዎችን እጥረት ለመቅረፍ በስፖርቱ ዘርፍ አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ለልዩ ልዩ የስፖርት አይነቶች አገልግሎት የሚውሉ በርካታ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪ ስፍራዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
በዚህም ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶችና ኮንፈረንሶች ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ይገኛል፡፡
ኢዜአ በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተወዳዳሪዎችን አነጋግሯል፡፡
አስተያየት ከሰጡን ተወዳዳሪዎች መካከል አትሌት ኩሳ ኃይሌ፤ ቀደም ሲል በቂ የልምምድ ቦታዎች በአቅራቢያችን ስለማይገኙ ለልምምድ ርቆ መሔድ ግድ ይል እንደነበር አስታውሷል፡፡
አሁን ላይ ግን በመኖሪያ አካባቢያቸው ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በመገንባታቸው ከእንግልት መዳናቸውን ጠቁሟል፡፡
ማዘውተሪያዎቹ ዘመናዊ ግብዓቶችን ያሟሉ በመሆናቸው ለሁሉም የስፖርት አይነቶች ምቹ መሆናቸውን አመላክቷል።
በመዲናዋ የተገነቡ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለዓመታት እንቸገርበት የነበረውን የልምምድ ቦታ እጥረት በዘላቂነት የቀረፉ ናቸው ሲልም ገልጿል።
አትሌት ቻላቸው ሙሌ በበኩሉ፤ መንግሥት ለስፖርት መሠረተ-ልማት ግንባታ የሰጠው ትኩረት ጤናማ እና አምራች ትውልድ ከመፍጠር ባለፈ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞችን ለማፍራት ያግዛል ብሏል።
መንግሥት በስፖርቱ ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት ለኛ ዐቅም እንዲሁም ለመጭው ትውልድ ደግሞ ተስፋ የሚሆኑ ናቸው ያለው ደግሞ አትሌት ማርታ ግርማ እና አትሌት አይናለም አየለ ናቸው፡፡