ቀጥታ፡

ብዝኀ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በመተግባር በገጠርም ሆነ  በከተማ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- ብዝኀ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በመተግባር በገጠርም ሆነ  በከተማ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል ሲሉ የድሬዳዋ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ገለጹ።

በብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ በስፖርታዊ ውድድሮችና በድጋፍ ሰልፎች የታገዘ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።



 
በሳብያን የከተማ ወረዳ በተካሄደ ቅስቀሳ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት፤ ብልጽግና ፓርቲ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ሰው ተኮር ልማቶችን ማሳካት ችሏል።
 
ለዚህም ብዝኀ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በመተግባር በገጠርም ሆነ  በከተማ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አንስተዋል።
 
ፓርቲው የፖለቲካ እሳቤውን ኅብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ላይ በመመስረት የጋራ ትርክትን ለመገንባት በትኩረት መሥራቱንም አስረድተዋል።
 
የተመዘገቡ ዘርፈ-ብዙ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ውጤቶችን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም ፓርቲው አበክሮ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።



 
በገጠር ክላስተር በተካሄደው ቅስቀሳ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሱልጣን አልይ ደግሞ፤  በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች የልማት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። 
 
በመሠረተ-ልማት፣ በግብርና ዘርፍ፣ በጤናና በትምህርት የተመዘገቡ ውጤቶች የሕብረተሰብን ማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ ማቃለላቸውን አስታውቀዋል።
 
የገጠሩ ወጣት በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሰማራት በኢኮኖሚ ራሱን ከመቻል ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም