ቀጥታ፡

የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር

ክልሎች፤ሚያዝያ 18 /2018 (ኢዜአ)፡-የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር

በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር የምንቃኝበት ነው። በዚህ ሳምንትም አንኳር የክልሎች ክንውኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ቀርበዋል።

የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጫ ማህተም!

ኢትዮጵያ የበጋ መስኖ ልማት ስራ መደባኛ ስራዋ ካደረገች ወዲህ አያሌ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ። ባለፉት ዓመታት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በእቅድ እና በቁርጠኝነት በመከናወኑ ከውጪ የሚገባ ስንዴ ቀርቷል፤ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጥረቱም ቀጥሏል። ከተረጂነት ወደ አምራችነት የሚደረገው ሽግግርም ዓመቱን ሙሉ በማልማት እየታጀበ ሲሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ ነው። በዚህ ውስጥ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል።

በተያዘው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ወሬርሶ ማሊማ፣ በጂዳ ወረዳ ሲባ ሲርቲ እና ቂምቢቢት ወረዳ ሰገሌና ደርማሙሳ ቀበሌ በኩታ ገጠም የለማ እና በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ የስንዴ ቡቃያ አስቃኝተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፎቶ ጋር ያያዙት መልዕክትም ''ይህ የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በምግብ ራስን የመቻል እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጫ ማህተማችን ነው'' ይላል።

ብሪክስ -- ከተሳትፎ ባለፈ መፍትሄ አቅራቢ

ከሳምንቱ አንኳር ጉዳዮች መካከል በባህር ዳር ከተማ ''የብሪክስ አሁናዊ አቅሞች እና የኢትዮጵያ የልማት ትብብር ትኩረቶች'' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው ጉባኤ አንዱ ነው። ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ከተሳትፎ ባለፈ መፍትሄ አቅራቢ በመሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑ ይታወቃል። የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድራፊዕ አባራያ በመድረኩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ሳትፎዋን በማሳደግ በጥናት ላይ የተመሰረቱ የተደራጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የሚጠቅሙ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

መድረኩም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በፈጠራና በቴክኖሎጂ እድገት ውስጥ የራሷን ድርሻ ለመወጣት የሚያስችላት የሁለትዮሽ ትብብር ጭምር የተካሄደበት፤ በብሪክስ ማዕቀፋ በተለይም በግብርና እና ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና መሰል ዘርፎች ልምድ የተሰጠበትም መሆኑ ተመላክቷል።

ማረም እና ማነጽ

የማረሚያ ተቋማት የሰብዕና እና የክህሎት ግንባታ ማዕከል እንዲሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት መሰጠቱ የተገለጸውም በዚሁ ሳምንት ነው። የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ “የማረሚያ ተቋማት ለሀገር ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የማረሚያ ተቋማት የሰብዕና እና የክህሎት ግንባታ ማዕከል ሆነው እንዲያገለግሉ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የመሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦት፣ ከማረሚያ ቤት የሪፎርም ሥራዎች እንዲሁም ከማረም የማነጽ ተሃድሶ ልማት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጉባኤው በልዩ ሁኔታ የመከረበት ነው።

ኢትዮጵያ ማምረቷን ቀጥላለች

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና የራስን አቅም የመገንባት ታሪካዊ ጉዞ እንደቀጠለ ነው። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል "ድሬ ታምርት ኢትዮጵያ ትበልፅግ" በሚል መሪ ሃሳብ በድሬዳዋ በተዘጋጀ የአምራች ኢንዱስትሪ ኤክሲፖ ላይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ በተደረገው ድጋፍና ክትትል እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። በንቅናቄው የተዘጉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ በማድረግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በጥራትና በስፋት እየተተኩ ነው ብለዋል። ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በማምረት፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም መሠረታዊ ውጤቶች ተገኝተዋል ነው ያሉት። ዘንድሮ ብቻ 13 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገቡ የውጭ ሀገራት ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በዘርፉ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውም ተገልጿል።

ውኃ ይበላል፤ ውኃ ይጠጣል

በኢትዮጵያ ቆላማ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች ውኃ የህልውና ጉዳይ ነው። በእርግጥ ለፍጡራን ሁሉ ውኃ ህይወት ቢሆንም በእነዚህ አካባቢዎች ግን ውኃ ይበላል፤ ውኃ ይጠጣል። በሳምነቱም በአፋር ክልል ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የአይሳኢታ አፋምቦ የብዙሃን መንደር እና የአይሳኢታ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ የተከናወነው ልማት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በተግባር ከመመለሱ በላይ፣ በየደረጃው ያለውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፤ መንግስት የውሃ ሽፋን አነስተኛ ለሆነባቸው አካባቢዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ በፕሮጀክቶች ታግዞ መስራት እንደሚገባ በጽኑ ያምናል፤ በተለይም የለውጡ መንግስት ለቆላማ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች በሰራው ስራ የውኃ ተደራሽነት በእጅጉ ማደጉን አንስተዋል።

ልምድ ልውውጥ እና ተሞክሮ -ለምክር ቤቶች

ሌላው ቅኝታችን በዚህ በተጠናቀቀው ሳምንት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤትና የዞን ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ መካሄዱን የዳሰሰ ነው። የጋራ የምክክር መድረኩ ዓለማ የልምድ ልውውጥና የልማት ሥራዎችን በመመልከት ተሞክሮ መለዋወጫ ነው።የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፤ መንግስት ሕዝቡ የሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የምክር ቤቶችን አደረጃጀት ማጠናከርና የክልሉ ሕገ መንግስት ያስቀመጣቸውን ኃላፊነቶች መፈጸም ይገባል ብለዋል።የመንግስት የልማት ኢኒሼቲቮች የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ በመሆናቸው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው መተግበር እንዲችሉ ምክር ቤቶች ያለሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተመልክቷል።

የጤና ልማት ስራ እስከ አክሞ ማዳን

የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ በሚደረግ ጥረት የአጋር ድርጅቶች አስተዋጾ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም የተመለከተው በዚህ ሳምንት ነው። ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጋር በመሆን በአርባ ምንጭ ከተማ ያስገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ መሰል የጤና ዘርፍ የልማት ስራዎች መንግስት በዘርፉ የያዘውን ውጥን ከማሳካት አንጻር እገዛቸው ትልቅ መሆኑን አንስተዋል።ማዕከሉ ማህበረሰቡ በቅርበት ሕክምና እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ ሲታከም ሊያወጣ የሚችለውን ወጪ ያስቀራል። ማዕከሉ የኩላሊት እጥበት ማሽኖች፣ የመድሃኒት ቤት፣ መኝታ አልጋዎችና የህክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሟልቶ የተገነባ መሆኑም ታውቋል።

የከተሞች ኮሪደር- ከቱሪዝም እስክ ኮንፍረንስ ማዕከልነት

በኮሪደር ልማት እጅግ ከተዋቡ እና ከደመቁ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ሀዋሳ አንዷ ናት። በሳምንቱ የከተማዋ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ማጠናቀቂያ የምስጋናና ዕውቅና እንዲሁም የአራተኛ ዙር የኮሪደር ልማትና የሐይቅ ዳርቻ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄዷል፡፡ የሲዳማ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ‎ሀዋሳ ከተማን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል በማድረግ ከተማዋ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን ርብርቡ ቀጥሏል ብለዋል። በቀጣይ ለሚከናወነው የኮሪደር እና የሐይቅ ዳርቻ ልማት ስራዎች እንደሚቀጥሉ አንስተው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋና ማህበራዊ ትስስር ይበልጥ የሚያጎላ መሆኑን ገልፀዋል። የከተማዋን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከልነት ለማጠናከር ሥራዎች በላቀ ፍጥነትና ጥራት መከናወናቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ምርጫ -የዴሞክራሲ መሰረት

ሳምንቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ከመጠናቀቁ በፊት መራጮች የምርጫ ካርድ ወስደው ለምርጫው ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹበትም ነበር። ኢትዮጵያዊያን መጪውን ጊዜ የተሻለ የሚያደርግላቸውን መንግስት ለመመረጥ ዝግጅታቸውን በተግባር እያረጋገጡ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም