ባለፉት 9 ወራት በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት 9 ወራት በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ አፈጻጸም ተመዝግቧል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፎች ውጤታማ አፈጻጸም መመዝገቡን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአሥተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሥራ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት፤ በከተማ አሥተዳደሩ የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያስቻሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ የዕቅድ አፈጻጸም ውጤታማ መሆኑን ጠቁመው፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከተያዘው ዕቅድ 96 በመቶውን መፈፀም መቻሉን ገልጸዋል።
የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም በቀሪ ወራት የትኩረት የሚሰጣቸው የተጀምሩ እና በዚህ ዓመት መጠናቀቅ ያለባቸውን ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የመዲናዋ ያለፉት አምስት ዓመታት የዕቅድ አፈፃጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተለይ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም የልማት አብዮት በአዲስ አበባ ከተማ እየተመዘገበ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም በአምስት ዓመቱ ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች በመንግሥትና በሕዝብ በጋራ ማከናወን መቻሉን ነው የገለጹት።
ከ480 ሺህ በላይ ቤቶች በተለያዩ አማራጮች በአምስት ዓመቱ መገንባታቸውን ጠቁመው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በፕሮጀክቶች ጥሩ አፈጻጸም መመዝገቡን ተናግረዋል።
አሁን በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት፣ ጥራትና ጊዜ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ የሚያስችሉ የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
ሌላው የትኩረት አቅጣጫ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ችግሮችን በመቀነስ የዋጋ ንረትን መከላከል መሆኑን አንስተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ በማድረግ በተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግሥት አገልግሎት ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
ሕዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግ በተሠራው ሥራ በከተማዋ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉንም ገልጸዋል።