ግብርናውን ከኋላ ቀር አሠራር አውጥቶ ለማዘመን የተጀመረው ቅንጅታዊ አሠራር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናውን ከኋላ ቀር አሠራር አውጥቶ ለማዘመን የተጀመረው ቅንጅታዊ አሠራር ይጠናከራል
ባሕር ዳር፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ግብርናውን ከኋላ ቀር አሠራር አውጥቶ ለማዘመን የተጀመረው ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
12ኛው ዙር የአማራ ክልል የግብርና ልማት ባለድርሻ አካላት የግንኙነት አማካሪ ካውንስል ጉባዔ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የቢሮው ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በጉባዔው ላይ እንዳሉት፤ ግብርናውን ከኋላቀር አሠራር በማላቀቅ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለገበያ የሚሆን ምርት ማምረት ይገባል።
ለዚህም የማምረት ዘዴን ማዘመን አስፈላጊ በመሆኑ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።
የጉባዔው ዓላማም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይተው ግብርናውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል የመፍትሔ ሐሳብ ማሰባሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
የአርሶ አደሩን ችግር በጥናት በመለየት፣ የምርምር ውጤቶችን በመተግበርና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ ምርታማነት ለማሳደግ ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
እስካሁን በካውንስሉ አቅጣጫ መሠረት በባቄላ፣ በምስርና በሌሎች የሰብል ዘሮች ላይ በተከናወነ ምርምርም ምርታማነትን መመለስ ተችሏል ብለዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰማኸኝ አስረዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፈው ጉባዔ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የምርምር ሥራ ተከናውኗል።
በዚህም የግብርና ምርታማነትን ከመመለስ ባለፈ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አበረታች ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።
የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን በማላመድና በማሰራጨት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዋና ፀሐፊ ጀጃው ደማሙ (ዶ/ር) ናቸው።
በተለይም አርሶ አደሩ ከኋላቀር የእርሻ ሥራ ተላቆ የሜካናይዜሽን እርሻን እንዲላመድና የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርግ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን አውስተዋል።