ታሪክን ለትውልድ ለማሻገር -አዲስ ስፖርት ፓርክ - ኢዜአ አማርኛ
ታሪክን ለትውልድ ለማሻገር -አዲስ ስፖርት ፓርክ
የአዲስ ስፖርት ፓርክ ታሪክን ለትውልድ ከማሻገሩ ባለፈ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ሚናው የጎላ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ጎብኚዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ ስፖርት ፓርክን መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው ይታወቃል።
አዲስ ስፖርት ፓርክ በውስጡ በዓለም የኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ በማድረግ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኙ 15 ጀግና የአትሌቲክስ ፈርጦችን የሚዘክር ሀውልቶችን በውስጡ ይዟል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ደረጃን ያሟሉ ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ፣የእግር እና የቅርጫት ኳስ፣የቴኒስና የሩጫ ትራክንና ሜዳዎችን ፓርኩ ውስጥ ከተካተቱ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በፓርኩ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉ ጎብኚዎችን አነጋግሯል።
ከጎብኚዎች መካከል ወጣት ሮቤል አብርሃም በሰጠው አስተያየት በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች ፓርኩን ማየቱን ገልጾ፥ በአካል በማየቱ ልዪ ስሜት እንደፈጠረበት ይናገራል።
በኢትዮጵያ በስፖርት ዘርፉ ለሀገር ትልቅ ታሪክ ያበረከቱ ሰዎችን ክብር በሚመጥን መንገድ የሚዘከሩበትን ምቹ መደላድል ለመፍጠር የተሰራው ስራ የሚበረታታ ነው ይላል።
በአዲስ ስፖርት ፓርክ ጀግኖች የሚታወሱበት ሃውልቶች መቆማቸው አሁን ላለነው ትውልድ ለሀገራችን የተሻለ ስራ በመስራት አሻራችንን እንድናሳርፍ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል ሲልም ገልጿል።
ወጣት ኢዘዲን አብዱልፈታ በበኩሉ፤ለኢትዮጵያን በጎ ስራን የሰሩ ሰዎችን በህይወት እያሉ እነሱን የሚዘክሩ ሃውልቶች መስራት ብዙም ያልተለመደ ነገር እንደነበረ በመግለፅ አሁን ላይ በአትሌቲክሱ የሀገርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረጉ አትሌቶችን ተገቢውን ክብር ለመስጠት ፓርኩ መሰራቱ ተገቢ መሆኑን ተናግሯል።
ለቀጣይ ትውልድም ስለ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣በመስኩ ላይ ምን አይነት አትሌቶች ነበሩን የሚለውን እንዲያውቁ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጿል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ያላትን ታሪክ ለሶስት ለልጆቻቸው ለማስጎብኘት በአዲስ ስፖርት ፓርክ መገኘታቸውን የገለፁት ደግሞ አቶ አረጋ በቀለ ናቸው።
በጉብኝታቸው ወቅት የታዋቂ አትሌቶችን ሃውልት ከማየት ባለፈ በዲጂታል መንገድ ስለ አትሌቶቹ መረጃን ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ በመኖሩ በቀላሉ ለልጆቻቸው ታሪክን መንገር እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ወላጆች ልጆች ስለ ሀገራቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሊጎበኙ የሚገባቸውን ቦታዎች ማስጎብኘት እንደሚገባቸውም መክረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መቶ አለቃ ገረመው ጨሬ በተለያዩ ኦሎምፒኮች ድልን የተጎናፀፉ አትሌቶችን የሚዘከሩበትን ፓርክ መንግስት መገንባቱ ተተኪ ስፖርተኞች እንዲፈሩ መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።
ማሙሽ ወንድሙ በበኩሉ፤ በአዲስ አበባ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች እየተስፋፋ መምጣቱ ለስፖርት ዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል በማለት ተናግሯል።
የስፖርት ፓርክንና ማዕከላት መስፋፋት ትውልዱ ጊዜያቸውን የማይጠቅም አካባቢ ከማሳለፍ ይልቅ እራሳቸውን፣ሀገራቸውን በሚጠቅም ቦታ እንዲያሳልፉ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።