ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር የውጭ ኩባንያዎችን ቀልብ እየሳበ ነው

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ያደረገችው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን በመፍጠር የውጭ ኩባንያዎችን ቀልብ እየሳበ መሆኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት የንግድ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ባከናወነችው የሀገር በቀል ኢኮኖሚና በተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች በርካታ ለውጦችን አስመዝግባለች፡፡

ግብርና፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አድርጎ በመስራት ኢትዮጵያ ጸጋዋን እንድትጠቀም በር ከፍቶላታል፡፡

ኢትዮጵያ ያደረገችውን ሁሉን አቀፍ ሪፎርምን ተከትሎ የዓለም የኢንቨስትመንት የትኩረት ማዕከል ሆናለች፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት የንግድ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ባህሩ ተመስገን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የንግድ ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከ200 በላይ የአውሮፓ ኩባንያዎችን በአባልነት የያዘ ነው፡፡

ምክር ቤቱ አንጋፋና አዳዲስ የሚገቡ ኩባንያዎችን በሥሩ በመያዝ በተሰማሩበት ዘርፍ የሚገኝባቸውን የፋይናንስና የሰው ሀይል ችግር ከመንግሥት ጋር በመሆን እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት የንግድ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በቅንጅት መሥራት የሚያስችል /Ethiopian Investment Deal Book/ አሳተመን ወደ ሥራ ገብተናል ብለዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ቢዝነስ ፎረም ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የአውሮፓ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለማየት መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚስቡ በርካታ ሪፎርሞች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ሪፎርሙ የዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ቀልብ እየሳበ ነው ብለዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ነባር አባላትን መከታተል ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወሳኝ የፖሊሲ እርምጃዎችን እና ግልጽ አሰራሮችን በመዘርጋት ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ መፍጠሯን ገልጸው፤መንግሥት ለግሉ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያለባቸው ጊዜ ነው ብለዋል፡፡

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #ENA

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም