ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው
ጅማ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ) የቱሪዝም ሚኒስቴር ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገለጸ።
ዛሬ በጅማ ከተማ "ፖሊዮን በጋራ እናጥፋ" በሚል መሪ ሐሳብ የ15 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ተካሂዷል።
በውድድሩ ላይ ከ10 ሀገራት የተውጣጡ እና ቁጥራቸው ከ4 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ተወካይ ተሾመ ተክሉ በዚሁ ወቅት፤ ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በየዓመቱ የተሳታፊዎች ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በክልል ከተሞች መካሄዱ ከተሞቻችንን ለማስተዋወቀ ያግዛል ብለዋል።
የፖሊዮ በሽታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ በሽታ መሆኑን የገለጹት የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ደግሰው ደርሶ በበኩላቸው፤ የሚታየውን የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍና የክትባት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በውድድሩ የጤና ተሳታፊዎች ፖሊዮን የማጥፋት መልዕክት በሩጫው ላይ አስተላልፈዋል።
የኢትዮቴሌኮም ደቡብ ምዕራብ ሪጅናል ዳይሬክተር ክፍሌ ካሳ ስፖርት ትውልድን በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ተቋማቸው እንደዚህ ያሉ ጠቃሚ ሀገራዊ ፕሮግራሞችን በመደገፍ በጋራ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ውድድሩን በወንዶች ጃፈር ጀማል እንዲሁም በሴቶች የግሌ እሸቱ ያሸነፉ ሲሆን፤ የሜዳሊያና ሌሎች ሽልማቶችም ተበርክቶላቸዋል።