ቀጥታ፡

እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት ናቸው

አሶሳ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በለውጡ መንግሥት እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት መሆናቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ከዳር እስከ መሃል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የልማት ትንሳኤ" በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።



 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አስር ኢብራሂም በዚሁ ወቅት፤ የለውጡ መንግሥት ብዝኀ የኢኮኖሚ ዘርፍን በመከተል ሀገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት እንዲኖራት በትኩረት መሥራቱን ተናግረዋል።



 
ለአብነትም የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ እና በዘርፉ የዜጎች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት እንዲጨምር ማድረጉን አንስተዋል።
 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በሪፎርሙ በመታገዝና ያለውን የተፈጥሮ ጸጋ በመለየት እያደረጋቸው ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች እመርታዊ ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ገልጸዋል።



 
የክልሉ ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም መንገሻ በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግሥት አዳዲስ እሳቤዎችን በመተግበር እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት፣ የፀጥታና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
ለውጡን ተከትሎም ክልሉ ያስመዘገበው የመልማት ዕድል በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊውና በፖለቲካው መስኮች ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ማስቻሉን ተናግረዋል።


 

ሀገራዊ ለውጡ በክልሉ ያስገኘውን የመሠረተ-ልማት፣ የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል ያሉት ደግሞ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዚያድ አብዱላሂ ናቸው።
 
እንደ ሀገር እየተከናወኑ የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሆኑ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን ነው አመራሮቹ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም