የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የወባ በሽታን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ጎንደር፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በክረምት መግቢያ ሊከሰት የሚችልን የወባ በሽታ ለመከላከል የአጎበር ሥርጭትና የኬሚካል ርጭት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ኃላፊ ምሳ ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ 10 ወረዳዎች እና 207 ቀበሌዎች ለወባ በሽታ ተጋላጭ ናቸው።
በዚህም መሠረት ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ቅኝትና ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሽታውን ቀድሞ ለመከላከልም ከ100 ሺህ በላይ የወባ ትንኝ መከላከያ የአልጋ አጎበር እየተሠራጨ መሆኑን ገልጸው፤ ከ200 ሺህ በሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች ላይም የኬሚካል ርጭት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በመኖሪያ ቤቶች የተደረገው የኬሚካል ርጭት ከ800 ሺህ በላይ ዜጎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
የጤና ባለሙያዎችም በአልጋ አጎበር አጠቃቀምና በኬሚካል ርጭት ወቅት መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ሕብረተሰቡን እያስገነዘቡ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
በማኅበረሰቡ ተሳትፎ "የአርብ ጠንካራ እጆች" በሚል መሪ ሐሳብ የወባ ትንኝ መራቢያ ስፍራዎችን የማጽዳትና የታቆረ ውኃን የማፋሰስ ተግባር መቀጠሉንም አስረድተዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የወባ ቁጥጥርና ሕክምና ተግባራት በወባ በሽታ የሚጠቁ ኅሙማን ቁጥር ከመቀነስ ባለፈ ሞትን ማስቀረት መቻሉንም አረጋግጠዋል።