ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞች ዕድገት የሚደነቅ ነው - የታላቁ ሩጫ በጅማ ተሳታፊዎች

ጅማ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዕየታየ ያለው የኢትዮጵያ ከተሞች ዕድገት የሚደነቅ መሆኑን የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ታላቁ ሩጫ በጅማ 2018 ተሳታፊዎች ተናገሩ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ ታላቁ ሩጫ በጅማ 2018 የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ተካሂዷል።



 
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ሳምሶን ዘለቀ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በጅማ ከተማ ለውጥ እጅግ መደነቃቸውን ተናግረዋል።

በፍጥነት እየተገነቡ ያሉ መሠረተ-ልማቶች የከተማዋን ዕድገት እያፋጠኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አንዳንድ የሀገራችንን ከተሞች ተመልክቻለሁ ያሉት አቶ ሳምሶን፤ ከዓመታት በፊት ከነበሩት ተለውጠው አሁን ላይ ፅዱና ማራኪ መሆናቸውን በመጥቀስ በዚህም መደነቃቸውን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ እና ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ጅማን የተመለከቱት ዮሐንስ አየልኝ፤ የከተማዋ ለውጥ እና የኮሪደር ልማት አስገራሚ መሆኑን ይናገራሉ።
 
ከተሞችን በማስዋብ እና በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዚህ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመላክተዋል።


 

በኢትዮጵያውያን የእንግዳ አቀባበልና በተመለከቱት የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት መደነቃቸውን የተናገሩት ደግሞ ፊንላንዳዊቷ ኪራ ፓካሪ ናቸው።
 
ጅማ ውብ ሆና መገኘቷን አድንቀው፤ ሌሎች ከተሞችም በዚሁ ልክ እየለሙና እየተለወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ጣሊያናዊው አልቤርቶ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ከዓመት በፊት ወደ ጅማ ከተማ መጥተው እንደነበር በማስታወስ፤ እየተገነቡ የነበሩ የተለያዩ መሠረተ-ልማቶች አሁን ተጠናቀው የከተማዋን ገፅታ መቀየራቸው እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደሚያስደስታቸውም አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም