የለውጡ መንግሥት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት አረጋግጧል - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ መንግሥት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት አረጋግጧል
አሶሳ፤ ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፦ የለውጡ መንግሥት የክልሉን የመልማት ዐቅም በማሳደግ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት አረጋግጧል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሠ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ከዳር እስከ መሃል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የልማት ትንሳኤ" በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሠ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የለውጡ መንግሥት የክልሉን የመልማት ዐቅም በማሳደግ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ አድርጓል።
ከለውጡ በፊት ክልሉ የዳር ተመልካች በመሆኑ የመሠረተ-ልማት እጦት እና ኢፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም በመኖሩ የመልማት ጥያቄ ሲነሳ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከለውጡ መንግሥት በኋላ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ እና ፀጋዎቹን ለይቶ በማልማት ሕብረተሰቡ ከሀብቱ ተጠቃሚ መሆኑን አንስተዋል።
በማዕድን ዘርፍ የታየው ለውጥ የኢኮኖሚ መሠረት በመሆኑ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማት እና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።
ለውጡ የክልሉን የፖለቲካ ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት በሀገር ጉዳይ ላይ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቅሰዋል።