ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት አቅም ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር በትብብር ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ዕድገትን እያፋጠነ ነው-ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት አቅም ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር በትብብር ላይ የተመሠረተ የኢኮኖሚ ዕድገትን እያፋጠነ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

በዓባይ ወንዝ ላይ የተበሰረው ሕዳሴም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የተሳሳተ ትርክት መስበር ያስቻለ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫን በመረቁበት ወቅት፤ የሀገራዊ ለውጡ የኢነርጂ ዘርፍ ሪፎርም የኢትዮጵያን የኃይል ሽግግር ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል ብለዋል።

በዚህም ከለውጡ በፊት የነበረው 4 ሺህ ሜጋ ዋት የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶች በማሳካት አሁን ላይ ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት በማሳደግ እመርታዊ ውጤት መምጣቱን አስታውቀዋል።

በኢነርጂ ዘርፍ የተሰራው ውጤታማ ሪፎርም የብሔራዊ የኃይል ቋት አቅርቦትና ሥርጭት አቅም በማጎልበት ህብረተሰቡን ከዋናውና አማራጭ የኃይል አቅርቦት ምንጮች ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ የኢነርጂ እመርታም ከራሷ አልፎ ለጎረቤቶቿ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በማፋጠን ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት መሳለጥ ገንቢ ሚና እየተወጣች ይገኛል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ የሪፎርም እመርታዊ ውጤት የኃይል አቅርቦት አቅምን መገንባት እያስቻለ ነው።

ለአብነትም በውስብስብ የግንባታ ሂደት የነበረውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በማጠናቀቅ የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት አቅም ከእጥፍ በላይ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅም የኢትዮጵያን የኃይል ሽግግር በማፋጠን ለጎረቤት ሀገራትን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ ትሩፋት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ በዝቅተኛ ዋጋ የምታቀርበው የኃይል አማራጭ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር ለማደግ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የጋራ ብልፅግናን የማፋጠን ፅኑ ፍላጎት አላት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ታሪካዊ ጠላቶች በሚሸርቡት ሴራ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን ሳትጠቀም እንድትቆይ አድርገዋታል ብለዋል።

በሀገራዊ ለውጡም ኢትዮጵያዊያን ሕዳሴን በዓባይ ላይ እውን በማድረግ የታሪካዊ ጠላቶችን የማይታለፍ የሚመስል ሴራ በድል መሻገር እንደቻሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ግዙፍ ፕሮጀክት ስኬትም ለአፍሪካዊያን የመነሳት ዘመን ምሳሌና ቀጣናዊ ኃይል አቅርቦት ማማ እንድትሆን ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዓባይ ላይ ለስኬት የበቃው የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከባሕር በር ለማራቅ የተሄደበትን የተሳሳተ ትርክት በመስበር በሁለቱ ውሃዎች ወግ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን የውሃ ሃብት ጸጋዎች በሚገባ በማልማት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም