የአሥተዳደሩ የበጀት ዓመቱ 9 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአሥተዳደሩ የበጀት ዓመቱ 9 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 18/2018 (ኢዜአ)፡-የከተማ አሥተዳደራችንን የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሥራዎች አፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀምሯል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላፉት መልዕክት፤ በበጀት ዓመቱ በእቅድ ከያዝናቸው ተግባራት 96 በመቶ መፈፀም ችለናል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው የግምገማ መድረክም ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ አመላክተዋል።
በመድረኩም፤ በበጀት ዓመቱ ለመፈፀም ካቀድናቸው ውስጥ በዘጠኝ ወራት በጥብቅ ክትትል የተከናወኑትን የምንገመግምበት እና በቀሪ ወራት የትኩረት ማዕከል አድርገን የምንፈፅማቸው ጉዳዮች ይነሳሉ ብለዋል።
በዚህም መሠረት፤ በመልካም አሥተዳደር ተለይተው ያልተመለሱትን ምላሽ በመስጠት ማጠናቀቅ፣ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ችግሮችን በመቀነስ የዋጋ ንረትን መከላከል፣ የገበያ መዛባት ችግሮችን መከላከል፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግሥት አገልግሎት የጀመርነውን ውጤታማ ሥራ በቀሪ ወራት በተሟላ ሁኔታ በማጠናቀቅና ወደ ሥራ ማስገባት የሉትም በግምገማው እንደሚነሱ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ቀሪ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ አድርጎ ወደ መሶብ ማስገባት፣ ተጀምረው በዚህ ዓመት መጠናቀቅ ያለባቸውን ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ የአፈፃፀም ግምገማ ማዕከላችን ይሆናሉ ብለዋል።
ባለፋት አምስት ዓመታት የእቅድ አፈፃፀማችን ከ90 በመቶ በላይ እያደገ መጥቶ በ2018 ደግሞ 96 በመቶ የደረሰበት ውጤታማ አፈፃፀም መኖሩን በመገምገም፤ ይህንን እያደገ የመጣ የመፈፀም ልምድ አጠናክረን መቀጠል እንድንችል በትኩረት እንገመግማለን ሲሉም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ነፃ፣ ተዓማኒና ገለልተኛ ሆኖ እንዲከናወን ሁሉም አመራራችን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ትልቅ ኃላፊነት መወጣት እንዲችል የግምገማ አቅጣጫን አስቀምጠናል ነው ያሉት።
የነበሩ ጥንካሬዎችን ማስቀጠል፣ ጉድለቶችን በመሙላት በቀሪዎች ወራት በላቀ መፈፀም የግምገማችን ማዕከል ይሆናል ብለዋል።